የይዞታ ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት ግጭቶች እንዲቀነሱ እያደረገ መሆኑ ተገለጸ

263

ነቀምቴ ሐምሌ 11/2011  በምስራቅ ወለጋ ዞን እየተሰጠ ያለው የገጠር መሬት የይዞታ ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት የሃብትና የንብረት ባለቤትነት ዋስትና ከመሆን ባሻገር ከወሰን ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ ግጭቶችን እንዲቀንሱ እያደረገ መሆኑን አርሶ አደሮች ገለጹ።

በዞኑ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ለ66 ሺህ 260 አባወራ አርሶ አደሮች የይዞታ ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት መሰጠቱ ተመልክቷል።

አርሶ አደር ጌታቸው ተመስገን በምስራቅ ወለጋ ዋዩ ቱቃ ወረዳ የጉቴ ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ የገጠር መሬት ይዞታ ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት ከመቀበላቸው በፊት በእርሻ ማሳ ወሰን የይገባኛል ንትርክ ምክንያት ከጎረቤቶቻቸው ጋር አለመግባባቶች ይፈጠሩ እንደነበር ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ተናግረዋል።

የይዞታ ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት ከተሰጣቸው ወዲሀ ግን የማሳቸውን ስፋት በግልጽ የሚታወቅ በመሆኑ ከግጭት ነፃ መሆን እንደቻሉ አስረድተዋል።

የይዞታ ማረጋገጫ ወረቀቱ የባለቤትነት ስሜቱን በማጎልበት ለምርትና ምርታማነት ማደግ ተነሳሽነታችን እንዲጨምር እገዛ እያደረገልን ነው ” ብለዋል።

የዚሁ ቀበሌ አርሶ አደር ደስታ ከበደ በበኩላቸው የገጠር መሬት ይዞታ ማረጋገጫ ወረቀት ማግኘታቸው የንብረት ባለቤትነት ዋስትና የሚሰጥ በመሆኑ ባላቸው አቅም በመስራት ሃብትና ንብረት እንዲፈሩ መነቃቃት እየፈጠረላቸው መሆኑን ተናግረዋል ።

ማረጋገጫ በተሰጣቸው መሬት ከባንክ ለመበደር እድል የፈጠረላቸው መሆኑንም አመልክተዋል።

በጊዳ አያና ወረዳ የገባ ጅማታ ቀበሌ አርሶ አደር ጋራዶ ኩሽ እንዳሉት ደግሞ የገጠር መሬት ይዞታ ማረጋገጫ ወረቀት የመንግስት የመሬት ገቢ ግብር በትክክለኛ መንገድ ለመክፈል ጠቀሜታው የጎላ ነው።

ያለ አግባብ ይባከን የነበረው መሬት በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውልና የሴቶችን እኩልነት ለማረጋገጥ እንደሚረዳ አስረድተዋል ።

በዞኑ የመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ጽህፈት ቤት የገጠር መሬት ይዞታ ማረጋገጫ ቡድን መሪ አቶ ዋቅቶላ ቅናጢ እንደተናገሩት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የገጠር መሬት ይዞታ ማረጋገጫ ወረቀት አስፈላጊ ነው ።

በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ለ66 ሺህ 260 አባወራ አርሶ አደሮች 96 ሺህ 300 የይዞታ ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት መሰጠቱን አመልክተዋል።

ባለፉት አራት ዓመታት ለ96 ሺህ 636 አርሶ አደሮች 247 ሺሀ 267 የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት እንዳገኙም አስታውሰዋል።

ከተሰጠው የይዞታ ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት መካከል 18 ሺህ 549 የሚሆኑ ሴቶች እንደሆኑ ተጠቅሷል።