የጠቅላይ  ሚኒስትሩ የአረጓዴ አሻራ ጉዞ ፋይዳ

622

በዮናስ ዘውዴ (AAU PhD candidate in philosophy)             

ዊሊያም ሼክስፒር “አንድ ሰው ተፈጥሮን መቅረብ ሲጀምር መላውን አለም ቤተሰብ ማድረግ የጀምራል” ይላል።  በዚህ የሼክስፒር ንግግር ውስጥ የምናየው ሰው ተፈጥሮን በቀረበ ቁጥር ከራሱ ወጣ ብሎ ስለሚያሰብ ሁሉንም ህይወት ያላቸውን ነገሮች ቤተሰብ ማድረግ እንደሚችል ነው።  ማርቲን ሉተር ኪንግ በበኩሉ በአንድ ወቅት እንዲህ ማለታቸው ይነገራል “አለም ነገ ወደ ትናንሽ ሀገራት እንደምትሄድ ባውቅም እንኳን ዛፍ መትከሌን አላቆምም”።

ካሊል ግብራር የሚባለውም ስለዛፎች እንዲህ ብሏል “ዛፎች  መሬት ሰማይ ላይ የሚፅፏቸው ግጥምች ናቸው።  ቪክተር ሁጎ ደግሞ “ ፍቅር እንደ ዛፍ ነው፥ በራሱ ፍቅርና አድነት ያድጋል፥ ስሮቹን ጥልቅ በመስደድ ትልቁን ምስል ይሰጠናል”። ሌሎችም ስመጥር የሆኑ ሰዎች ስለ ዛፍ ብዙ ንግግሮችን አድርገዋል።

እነዚህ ሁሉ የሚያሳዩን ዛፎችና ችግኝ በተለያዩ ሀገራትና ጊዜ የሰዎች መወያያ ሀሳብ እንደነበሩ ነው። የገዘፈ የሀሳብ ልዕልነታቸው ህይወትን፣ እድገትን፣አብሮነትን፣ ሰላም፣አንድነትን ተፈጥሮን የማስተሳሰር ጉልበት ስላላቸው የሰዎች የውይይት ማዕከል ባይሆኑ ነበር የሚገርመው።

በኛም ሀገር በተለያየ ጊዜ ስለ ዛፎችና ችግኝ ተከላ በተለይ በከፍተኛ አመራሮች የውይይት መድረኮች ነበሩ።  ሁሉም የችግኝ ተከላ መርሀ ግብር ተፈጥሮን ከማከም እይታ ብቻና ስለሆነና በሲስተም የተደገፈ ስላልነበረ ህዝቡ የራሴ ብሎ ሊወስደውና ቁርኝነቱን ጠንካራ ሊያደርግ ስላልቻለ ውጤታማ ሲሆኑ አልታዩም።

በኢትዮጵያ አብዛኛው የሰዎች ህይወት (ቤት መስሪያ፥ ለሀይል ማመንጫ ወዘተ) ከደን ጋር ስለተያያዘ ህዝቦች በተለያዩ ምክንያቶች ደኖችን እየቆረጡ ይጠቀማሉ። ነገር ግን ተፈጥሮን የማከሚያ ዘዴ ወዲያውኑ ችግኞችን መትከል ቢሆንም፤ በሰዎች እና በተፈጥሮ መሀል የነበረው ቁርኝነት ጠንካራ ስላልነበረ የተሰጠንን የደን ሽፋን ለሚቀጥለው ትውልድ ልናስቀጥል አልቻልንም ነበር። ዛሬ ግን ከትናንቱ መማር የግድ ይላላል።

ለችግኞች ፍቅር ሲኖረንና ለነሱ ያለን እይታ ሲሰፋ ዛሬ የምንተክለው ችግኝ የዛሬ 10፣ 20፣ 50፣ አመት እያለ ከኛ አልፎ ለሚቀጥለው ትውልድ ማሰባችንን ከምናሳይበት አሻራችን አንዱ ይሆናል። በተጨማሪ በችግኝ ተከላ ተሳትፏችን መጪው ትውልድ ስለተፈጥሮ ጥበቃ ያለንን ቀናዊ አስተሳሰብ ሰፋ አድጎ ያያል። ለአካባቢ ጥበቃ የሚቆረቆሩ አክቲቨስቶች እንደሚሉት የመጀመሪያው ችግኝ የሚተከልበት ጊዜ የዛሬ 20  አመት ቢሆንም ሁለተኛው ተመራጭ ጊዜ ግን ዛሬ ነው ይላሉ።

ለዚህም ይመስለኛል ጠቅላይሚኒስት ዶ/ር ዐብይ አህመድ በክረምቱ 4 ቢሊዮን ዛፎችን የመትከል አላማ የአመራራቸው አሻራ እንዲሆን አድርገው አበክረው እየሰሩ ያለው። እኔ እደሚመስለኝ ቁጥሩ ዝም ብሎ የመጣ አይደለም። አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ ተነስቶ የተራቆተውን የደን ሽፋናችንን ለማነቃቃት የግድ የዛን ያህል ስለሚያስፈልግ ይመስለኛል።

በሀገር ደረጃ ይህን ያህል የችግኝ ተከላ ሲታቀድ የመጀመሪያ ስለሆነ በመጀመሪያ ሀሳቡ ሲተዋወቅ ብዙን ሰው ግራ ያጋባ ነበር። መጀመሪያ መነጋሪያ የሆነው ከቁጥሩ መብዛት የተነሳ ማን ሊንከባከብ ነው የሚል ነበር።  ቁጥሩን ካየነው የህዝብ ብዛት 100 ሚሊዮን ብለን እንኳን ብንወስደው እያንዳንዱ 400 ችግኞችን መትከል አለበት ማለት ነው። ያልተለመደ አሰተሳሰብን በአንዴ እንደዚህ በዛ ብሎ ሲመጣ ስጋቱ ተገቢ ነው።  ነገር ግን የቁጥሩ ብዛት ያን ያህል የሚያሳስብ አይደለም። ለእኔ የጠቅላይሚኒስትሩ እይታ ተፈጥሮን ከማከም ያለፈም ይመስለኛል። ሀሳቡን ሰፋ አድርገን ካየነው በወሰንና በድንበር ምክንያት የዜጎችን የርስ በርስ ግጭቶች የማብረድ ጉልበት ያለው ይመስላል። በዛሬው በዚች አጭር ጽሁፌ የጠቅላይሚኒስትሩ የአረንጋዴ አሻራ ጉዞ ፋይዳውን ከተለያየ አቅጠጫ ለመቃኘት እሞክራለው።

ዛፎች ከሚሰጡት ብዙ ጥቅም የተነሳ ተፈጥሮን የሚወዱ ሰዎች እውነተኛ ህይወት ያለው ዛፍ በመትከል ውስጥ ነው ይላሉ። ከችግኝ ተከላ ጀምሮ የዛፎች የእድገት ጉዞ ካየነው ልክ እንደ ህፃን ነው። በሀሳብና በብዙ ህይወት ተሞልቶ እድገታቸው ለሚኖረው ሰው ተስፋ፥ የተለየ እይታ፥ ጥንካሬ፥ ብርታት እና ሌሎች ነገን በተስፋ እንዲያዩ መሰረት የሚሆኑ ምናባዊ እይታዎች  ስለሚሰጡን ይመስለኛል፤ እወነተኛ ህይወት ዛፍ በመትከል ውስጥ ነው ያለው የሚሉት።

እንደምናውቀው ለመኖራችን ዋስትና የሆኑት ዛፎች ለእኛ አየር ሲሆኑን እኛም እነሱን እንተነፍሳለን። ይሄንን ማን ይረሳዋል ልትሉ ትችላላችሁ ። ልክ ነው ይህንን ሁላችንም የምንረሳው አይመስለኝም። ስለዚህ ዛፎችንና ችግኝ ተከላን ስናስብ ሁላችንም ልክ እንደምንተነፍሰው አየር እያሰብናቸው እስከ መጨረሻው እስትንፋስ ድረስ በተሻለ መጠን እንድንወዳቸው ነው ሀሳቡን ያነሳሁት ።

ዛፎች ደስታን ለመፍጠር ካላቸው አቅም የደስታ ዋና ምንጮች ናቸው ይባላል። ብዙ ጥናቶች እንደ ሚያሳዩት ዛፎችና አረንጓዴ ቦታዎች አዕምሮ ላይ የሚፈጠርን የኑሮ ጫና እንደሚቀንሱ ነው። ለዚህ ትልቁ ማሳያ የሚሆነው አረጓዴ ልማት በብዙ የአዕምሮ ጤና ማገገሚያ እንደ አንዱ ህክምና ተደረጎ መወሰዱ ነው። በተለይ በሱስ ለሚሰቃዩ የአዕምሮ ህምመተኞች በማገገሚያ ጊዚያቸው ከተፈጥሮ ጋር እንዲቆራኙ ይደረጋል። ቁርኝቱ ከሱሱ ይልቅ ተፈጥሮ ላይ የበለጠ ትኩረት እንዲያደርጉ ስለሚረዳቸው ደስታን ወደራሳቸው በማምጣት ከገቡበት ሱስ በሂደት እንዲያገግሙ እደሚረዳቸው ጥናቶች ያሳያሉ።

ሀሳቡን ትንሽ ገፋ ለማድረግ እንደሚታወቀው አውሮፓና አሜሪካ ከኛ በተለየ ፎል (fall) የሚባል ወቅት አላቸው። በዚህን ወቅት ዛፎች ቅጠላቸውን አራግፈው የበረዶ ጊዜያቸውን የሚያተናግዱበት ነው።  በዚህ ወቅጥ ብዙ ሰዎች የአዕምሮ ጫና ውስጥ ይገባሉ። ብዙ ጥናቶችም እደሚያሳዩት በአንዳንድ ሀገሮች በተለይ በእስካዲኒኔቪያ ሀገሮች ራስን የማጥፋት (suicide) የሚበዛው በዚህ ወቅት እንደሚሆን ይዘገባል። በተለይ እንደ እኔ አብሯቸው ኖሮ ላየው ዛፎቹ ቅጠላቸው ከመርገፉ በፊት ሰዎች ላይ የሚታየው የደስታ ስሜት ከፍተኛ መሆኑ በግልፅ ይታያል።  ስለዚህ ይሄ የሚያሳየው ዛፎች ሲያብቡ በሰዎች አዕምሮ ውስጥ አዎንታዊ መልዕክቶችን ስለሚልኩ ሰዎች በተሻለ መጠን ማህበራዊ ህይወታቸውን እንዲያስኬዱ ይረዳል። በተለይ ይሄ በትላልቅ ከተሞች እንደ ኒውዮርክ ከተማ አይነቶች የኑሮ ጫና ከፍተኛ በሆነበት የፎል ወቅት አልፎ ክረምቱ ሲመጣ ሰዎች ከሚገባው በላይ ሲደሰቱና ብዙ ጊዜያቸውን ከቤት ውጪ ሲይሳልፉ ይታያሉ።

ዛፎች ለህይወት ከሚሰጡት ሰፋ ያለ ጥቅም ትልቁን ድርሻ የሚወስደው ለአካባቢ ጥበቃ ያላቸው አዎንታዊ ድርሻ ነው። እንደሚታወቀው ከባቢ አየራችን በተለያዩ ጋዝ (gas) የተሞላ ነው። በተለይ ከተለያዩ ፋብሪካዎች የሚወጡት በካይና በረጅም ጊዜ ለጤና ጠንቅ የሆኑ ንጥረ ነገሮች ከባቢ አየሩን ይይዙታል። ዛፎች በተፈጥሮ ከባቢን አየር ለአየር ንብረት መለወጥ ጠንቅ የሆኑ ጋዞችን የማፅዳት አቅም አላቸው። በተፈጥሮ ኦክሲጅንን (oxygen) ለማመንጨት ሲሉ ናይትሮጅን ኦክሳይድ (nitrogen oxide)፥ ካርቦን ዳይ ኦክሳይድ (carbon dioxide)፥ ኦዞን (ozone) እና አሞኒያን (ammonia) ስለሚጠቀም በሂደት እነኝህን ጋዞች ከአየር ላይ በመሰብሰብ የካርቦን (carbon) ብዛት ከባቢው አየር ላይ እንዳይበዙ ይከላከላሉ።  ካርቦንን ጨምሮ እነዚህ ጋዞች ግሪን ሃውስ ጋዝ (greenhouse gas) በመባል ይታወቃሉ።  የነሱም በአየር ላይ መብዛት ለአየር ሙቀት መጨመር ትልቁን ሚና ይጫወታል። የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት በተለያዩ ሰው ሰራሽ ምክንያቶች በከባቢ አየር ውስጥ የሚገኘውን የካርቦን መጠን ዛፎች ሁለት ሦስተኛውን መሰብሰብ እንደሚችሉ ነው ።

በብዙ ቦታዎች እደሚታየው ከአየር ሙቀት መጨመር ጋር ተያይዞ የአየር ንብረት መዛባት መሬት ላይ ትልቅ ጫና እየፈጠረ ነው።  ለምሳሌ፡ አንዳንድ ቦታዎች ከመጠን በላይ ዝናብ መጣልና ህዝቡን ለተለያዩ ከባድ ጎርፍ ማጋለጥ፥ በሌላ ቦታ ዝናብ ወቅቱን ጠብቆ ባለመዝነቡ እና የዝናብ መጠን በመቀነስ ስዎችን ለተለያዩ ችግሮች ማጋለጥ ፥  በተወሰኑ ቦታዎች ደግሞ ከፍተኛ ሙቀት ወይም ከፍተኛ ቅዝቃዜ በማምጣት በሰዎች የለት ተዕለት ኑሮ ላይ ጫና መፍጠሩ በግልፅ እየታየ ነው።  በተለይ ጫናው በደንብ በተካታታይ መታየት የጀመረው ካለፉት አምስት እና ስምንት አመት ወዲህ ነው። ስለዚህ  አንድ ሀገር የደን ሽፋኗን ማስቀጠል ካልቻለች ህዝቦቿ ለተለያዩ የተፈጥሮ አደጋዎች መጋለጣቸው አይቀርም።

በዚህ በያዝነው ክረምት ብቻ በተለያዩ አካባቢ የሚሰሙ ዜናዎች እንደሚያሳዩን ከሆነ  በየሳምንቱ ከአየር ንብረት መቀየር ጋር ተያይዞ ህዝቦች ለተለያዩ አደጋ እየተጋለጡ መሆናቸው ነው። ባሳለፉነው ወር ከአውሮፓ ጀምሮ የሙቀት መጠን በከፍተኛ በመጨመሩ የሰው ህይወት ጠፍቷል። ለምሳሌ በህንድ ወደ 100 ሰዎች መሞታቸው ተዘግቧል። በኤዢያ ዝናቡ ከመጠን በላይ በመዝነቡ ህዝቦችን ለተለያዩ አደጋዎች አጋልጧል።  በኛም ሀገር በወቅቱ በቂ ዝናብ ባለመዝነቡ በቂ ውሃ ግድቦች ውስጥ ስላልገባ በቂ ሀይል ማመንጨት ስላልቻሉ ወደ ፈረቃ ለመግባት ተገደን  ነበር። በተመሳሳይ በቂ ዝናብ ባለመዝነቡ በህንድ በቸናይ ከተማ ህዝቦች የሚጠጡት ዉሀ አተው እየተሰቃዩ ይግኛሉ። የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያዎች ይሄንን በተለያዩ አካባቢ የሚታዩት የተፈጥሮ ችግሮች በሰው ሰራሽ ምክንያት ከሚፈጠር የአየር ንብረት መለወጥ ችግር ነው ብለው በመደምደም ሀገሮች ለመፍትሔው እንዲረባረቡ ጥሪያቸውን እያቀረቡ ይገኛሉ።

የአየር ንብረት መለወጥ አደጋነትን በመገንዘብ ከግሪክ፥ ጣሊያን እስከ አውስትራሊያ እና ሳውዝ ኮሪያ እስከ አሜሪካ ያሉ ትላልቅ ከተሞች ችግኞችን ወደ መትከል ተመልስው አጠንክረው ይዘውታል።  የደቡብ ኮሪያ ዋና ከተማ በቅርቡ  በርከት ያሉ ችግኞችን የተከሉ ሲሆን፤ በተመሳሳይ ሚልበርን በአውስትራሊያ በጣራ ላይ የሚገኙትን አረጓዴ ተክሎች በ2040 በ40% ለማሰደግ እየሰሩ ይገኛሉ።  በሌላ በኩል ከፍተኛ ሙቀትን ከመከላከል አንፃር አቴንስ በግሪክ ብዙ ዛፎችን ለመትከል አቅደው እየሰሩ ነው።  ሚላን በጣሊያን እስከ 2030 ሶስት ሚሊዮን ዛፎችን ለመትከል አቅደው እየሰሩ ነው።  በአለማችን ታላቋ ከተማ ኒውዮርክ ከተማ (New York City) 1 ሚሊዮን የሚሆኑ ዛፎችን ለመትከል በከተማዋ የደን ሽፋን ያነሰባቸውን ቦታ መርጠው ጨርሰው ወደ ስራ ለመግባት በዝግጅት ላይናቸው ። በአሀጉራችንም ናይጄሪያ እና ሲኔጋል ከስራ ፈጠራ ጋር አያይዘው ሰዎች አትክልት የሚሰጡ ዛፎችን በብዛት እንዲተክሉ መንግስት ድጋፍ እያደረገላቸው ይገኛል። የነኚህ ከተሞች የአረጓዴ አካባቢን (green space) የማስፋት ንቅናቄ የዛፎችን ለአካባቢ ንብረት ጥበቃ ያላቸው ፋይዳ አጉልቶ የሚያሳይ ነው።

በእኛም ሀገር በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጠናክሮ የቀጠለው አረንጓዴ አሻራን የማስቀመጥ ዘመቻ የአሀኑን የአለም ነባራዊ  ሁኔታ በደንብ ያገናዘበ ነው። በዚህ ክረምት ብቻ 4 ቢሊዮን ዛፎችን በመትከል ሀሳቡ በቀጥታ በሰው ሰራሽ ምክንያት የሚመጣውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከል የራሱን አስተዋጽኦ ያደርጋል። በሂደትም ህዝብን ከላይ ከተጠቀሱት ከተለያዩ ተፈጥራዊ አደጋዎች በመከላከል ህዝቦች በምግብ እራሳቸውን እዲችሉና ጤናቸውን እንዲጠብቁ የራሱን አስተዋጽኦ ያደርጋል። በተጨማሪም በሰው ሰራሽ ምክንያት የሚመጣውን የአየር ንብረት ለውጥን መታደግ ከሰዎች ውጪ ሌሎች ህይወት ላላቸው ነፍሳት በሙሉ አካባቢን ለነሱ አመቺ በማድረግ ሥነምህዳር (ecosystem) በማመጣጠን ብዝሃብት  እንዳይጠፋ ይከላከላል።

ከችግኝ ተከላው ጋር ተያይዞ የሚሰሩ ስራዎች ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ችግኝ ተከላውን ተፈጥሮን ከማከም ባሻገር ያዩት ይመስለኛል። እንዳየነው ችግኞችን እንደ አዎንታዊ ሀይል በመጠቀም ጎረቤት ሀገራትን የበለጠ ለማስተሳሰር ችግኝ አብሯቸው እንዲተክሉ በማድረግ ጎረቤት ሀገራት የራሳቸውን አሻራ እንዲያቀምጡ እያደረጉ ነው። ጎረቤት ሀገራት ላይ መሰረት ያደረገ የውጪ ፖሊሲ ለሚከተል ሀገር ጥሩ የትስስር ማጠንከሪያ መንገድ ይመስሳላል። በሀገር ውስጥም ጠንክረው ህዝቡን በማሳተፉ በህዝቦች መካከል የበለጠ ትስስር እንዲኖርና ህዝቦች ብዙ አንድ የሚደርጋቸው እሴቶች እንዳሏቸው እያሳዩ ነው። ከላይ እደተገለፀው ዛፎች በተለየ ሁኔታ ከተፈጥሮ ጋር ትልቅ ቁርኝነት ስላላቸው በውስጣቸው ሁለተናዊ እሴቶችን (universal values) አቅፈው ስለያዙ ከሀገር አልፈው የአለምን ህዝብ አንድ የማድረግ ሀይል ስላላቸው ነው።

የተለያዩ የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቾችንና አጥኚዎች የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጅማሮ በጥሩ እያዩት ይገኛሉ። በመስከረም ወር በሚደረገው አመታዊ የተባበሩት መንግስታት የመሪዎች ስብሰባም የአየር ለውጥ አንዱ አጀንዳቸው ነው። ኢትዮጵያ እንደ ሀገር የጀመረችው የ4 ቢሊዮን ችግኞች ተከላ የአለም የአየር ለውጥን ከመታደግ አንፃር በጥሩ እደሚነሳ ምንም ጥርጥር የለኝም። ሁላችንም እንደምናውቀ ዛፎች በባህሪያቸው ብዙ እድሜ ይኖራሉ። ስለዚህ ዛሬ ላይ ሆነን የምንተክለው ችግኝ የዛሬ 20፥ 50፥ 100 አመትን እያሰብን ነው። ስለዚህ በሂደቱ ስንሳተፍ በልጆቻችን እና በልጅ ልጆቻችን ተወቃሽ እንዳንሆን ይረዳናል። ሥራው ከሀገር አልፎ አለምን የማዳንና በመጥፋት አፋፍ ላይ ያሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ነፍሳትን (species) የማዳን ስራ ስለሚሆን ለጥሪው ምላሽ በመስጠት በሀገራችን፥ በአህጉሩ እና በአለም ላይ የራሳችንን አሻራ እናስቀምጥ።

አራት ቢሊዮኑን ለማሳካት በተለያዩ ጊዜ የሚደረጉ ጥሪዎች ይኖራሉ፤ ለምሳሌ የፊታችን ሀምሌ 22፣ 200 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል እቅድ አለ። ስለዚህ በመርሃ ግብሩ ላይ መሳተፍ ግድ ይላል። አስተባባሪዎቹም ችግኞቹን ከመሬትና ከአየር ንብረቱ ጋር የማጣጣም  ስራና ደኖች የተራቆቱ ቦታዎችን በመለየት ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ሂደቱን ውጤታማ ለማድረግ ትልቅ ስራ እየሰሩ ይመስላኛል። ከመትከል ባለፈ ችግኞቹም እንዲያድጉ የተለየ አቅጣጫ ተነድፎለት መጀምር ብቻ ስይሆን ጨርሰን ለውጤት ማብቃት እንደምንችል በደንብ ተንከባክበናቸው ምስክረነታችንን ማሳየት ያስፈልጋል።