በጀቱ ለሀገሪቱ እድገትና ለውጥ እንዲውል ያለፉት አመታት ክፍተቶች ሊስተካከሉ ይገባል

71
ሐምሌ 11/2011 ለ2012 በጀት አመት የተመደበው በጀት ለታለመለት አላማ እንዲውል ከዚህ በፊት የነበሩ ችግሮች እንዳይደገሙ መስራት እንደሚገባ አንድ የምጣኔ ሃብት ባለሙያ ተናገሩ፡፡ መንግስት ለእድገት ተኮር ዘርፍ የመደበው በጀት በአግባቡ ስራ ላይ ከዋለ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ የሚያሳድግ በመሆኑ ችግሮች ሲያጋጥሙ ፈጥኖ ማስተካከል እንደሚገባ ባለሞያው ጠቅሰዋል፡፡ ለ2012 በጀት አመት የተመደበው በጀት ለታለመለት አላማ እንዲውል ከዚህ በፊት የነበሩ ችግሮች እንዳይደገሙ መስራት እንደሚገባ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት በግል ፕሮጀክቶች አመካሪነት ስራ ላይ የተሰማሩ አቶ ሰለሞን ግርማ ናቸው፡፡ ሀገሪቱ ባለፈው አመት በሰራችው የዲፕሎማሲ ስራ ተፈጥሮ ከነበረው የምንዛሬ እጥረት የሚያስወጣትን ብድርና እርዳታ ማግኘቷ መልካም ስኬት ነበር ያሉት አቶ ሰለሞን   በቀጣይም ትኩረት ሰጥቶ መስራት ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡ መንግስት ለወጭ ንግድ የሰጠው ትኩረት ግልጽ አይደለም ያሉት ባለሙያው፤ በዘርፉ ላይ የሚነሱ ብልሹ አሰራሮችን በማስተካከልና ከጥሬ እቃ ላኪነት ደረጃ በደረጃ እሴት ወደ ተጨመረበት ምርት ማሳደግ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ  ወሳኝ መሆኑንም ጠቅሰዋል። መንግስት ከውጭ ሀገራት በሚበደራቸው የብድር አይነቶች ላይ እያደረገ ያለው ማስተካከያ ሀገሪቱ ወደ ብድር ቀውስ ውስጥ የበለጠ እንዳትገባ የሚያደርግ ነውም ብለዋል። ባለፉት አመታት መንግስት ለሚሰራቸው ፕሮጀክቶች ከመረጣ ጀምሮ ዘርፈ ብዙ ችግሮች የነበሩበት በመሆኑ በመዘግየታቸው ምክንያት የሚፈለገውን ጥቅም መስጠት ባለመቻላቸው በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ  ጉዳት ማድረሳቸውን ተናግረዋል። በበጀት ዓመቱ አዲስ የሚጀመሩት ፕሮጀክቶች በተሰጠው አቅጣጫ መሰረት ክትትልና ቁጥጥር በማድርግ በተቀመጠላቸው ወቅትና ወጪ እንዲጠናቀቁ መስራት  እንደሚገባም ነው ባለሙያው የተናገሩት። ለካፒታል ወጪ የተመደበው 34 በመቶ በጀት በአግባቡ ሥራ ላይ በማዋል ለአገሪቱ እድገት ወሳኝ ድርሻ እንዲኖረው እና  ለሀገር ውስጥ ተቋራጮች ማበረታቻ የሚሰጡ ፕሮጀክቶች በመዘግየት የሚያደርሱትን ሀገራዊ ጉዳት በማረም፤ አቅምን እና እውቀትን በማገናዘብ በአዳዲ ፕረጀክቶች ላይ ማሳተፍ እንደሚገባም መክረዋል። የሀገር ውስጥ ተቋራጮች ተቀናጀተው አቅማቸውን ከፍ የሚደርጉበትን ሁኔታ እንዲፈጥሩም መንግስት ድጋፍ ሊያደርግላቸው እንደሚገባም ነው አቶ ሰለሞን የጠቆሙት። አሁን የተመደበው በጀት ሀገሪቱ ካላት ህዝብ አንጻር ዝቅተኛ መሆኑን የገለጹት ባለሙያው፤  የግብር መሰረቱን በማስፋት ገቢን በማሳዳግና  ለኦዲት ግኝቶች ትኩረት ሰጥቶ ተጠያቂነትን ማስፈንም ከተቻለ በጀቱ ለታለመለት አላማ  ሊውል ይችላል ነው ያሉት። የመንግስት መስሪያ ቤቶች ለቀጣይ አመት ይቀነስብናል በሚል አስተሳሰብ በሰኔ ወር በጀታቸውን ለመጨረስ ያለእቅድ የሚያወጡት ወጪ ሀገርን ለሀብት ብክነት እየዳረገ በመሆኑ አሰራሮች ሊሻሻሉ እንደሚገባል ተናግረዋል። የምክር ቤት አባላት በፕሮጀክቶች ላይ ክትትል በማድርግ ችግር ያለበትን ለይተው  ፈጣን የማስተካከያ እርምኛ  መውሰድ አለባቸው ያሉት ባለሙያው፤ ባለፉት አመታት ግዙፍ ፕሮጀክቶች በወቅቱ ባለመጠናቀቃቸው ከፍተኛ የገንዘብ ብክነት ማስከተላቸውንም ተናግረዋል፡፡ በሚሰሩ የመንግሰት ፕሮጀክቶች ላይ የዘርፉ ምሁራን አስተያየት የሚሰጡበት ሁኔታ  ሊመቻች ይገባል ያሉት አቶ ሰለሞን፤ ባለፈው በጀት ዓመት የተከናወነው የግብር ንቅናቄ ፕሮግራም የባለቤትነት ስሜት እንዲፈጠር በማድረግ ውጤት በማምጣቱ በሌሎች ዘርፎችም በመስራት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ማነቃቃት እንደሚቻልም አብራርተዋል። እንግሊዝና አሜሪካን ጨምሮ ያደጉት በርካታ የአለም ሀገራት ከተለያዩ ሀገራት በሚመጡ ኢንቨስተሮችና እውቀት በመሆኑ፤ የውጭ ባለሃብቶች ወደ ኢትዮጵያ በስፋት  በመምጣት መዋለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ማድረግ እንደሚገባም ሙያዊ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። የኢፌዲሪ መንግስት ለ2012 በጀት አመት 386 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር አመታዊ በጀት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጸድቋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም