የሱዳን ወታደራዊ ሽግግር ምክር ቤት እና የነፃነትና የለውጥ ኃይሎች ስምምነት ፈጸሙ

61
ሐምሌ 10/2011 (ኢዜአ) የሱዳን ወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤት እና የነፃነትና የለውጥ ኃይሎች የፓለቲካ ስምምነት ተፈራረሙ። ስምምነቱን የፈረሙት ኢትዮጵያና የአፍሪካ ህብረት ሁለቱን አካላት ለማቀራረብ ያደረጉትን ጥረት ተከትሎ ነው። የሱዳን ወታደራዊ ሽግግር ምክር ቤት እና የነፃነትና የለውጥ ኃይሎች  ዛሬ የፓለቲካ ስምምነት መፈራረማቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በላከው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል። ስምምነቱ የተፈረመው የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ሕብረት የጋራ አደራዳሪዎች ባቀረቡት የስምምነት ሀሳብ ላይ ከተወያዩ በኋላ ነው። የተፈረመው የፖለቲካ ስምምነት የመንግስት አወቃቀር እና በሽግግሩ ወቅት ትኩረት የሚሰጣቸውን ጉዳዮች የሚገዛ ሰነድ ነው። በሱዳን የተከሰተውን ሕዝባዊ ተቃውሞና የመንግስት ለውጥ ተከትሎ ወታደራዊ ሽግግር ምከር ቤት እና የነፃነትና የለውጥ ኃይሎች መካከል አለመግባባት ተከስቶ ነበር። ይህን ተከትሎ ሁለቱን አካላት ለማቀራረብና የሲቪል መንግስት ለመመስረት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ያስጀመሩት ጥረት ከአፍሪካ ህብረት ጋር በተደረገ የተቀናጀ ጥረት ውጤት ማስገኘቱ በመግለጫው ተጠቅሷል። የድርድር ሂደቱ የአፍሪካን ችግር በአፍሪካዊያን መፍታት እንደሚቻል እና ኢትዮጵያ በቀጠናው ሠላምና ጸጥታን ለማስፈን ያላትን ቁርጠኝነት በድጋሚ ያረጋገጠችበት ነው ተብሏል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም