የሀዋሳ ከተማ የቅርጫት ስፖርት ክለብ ከስፔኑ ባርሴሎና አቻው ድጋፍ አገኘ

57
ሀዋሳ ሐምሌ 10/2011 (ኢዜአ) በስፔን ባርሴሎና የሚገኘው የአሴዴ ጋቫ ቅርጫት ኳስ ስፖርት ክለብ ለሀዋሳ ከተማ ስፖርት ክለብና በሥሩ ለሚገኙ የቅርጫት ኳስ ፕሮጀክት ቡድኖች 430 ሺህ ብር የሚገመት የትጥቅና የሥልጠና ድገፍ አደረገ፡፡ ክለቡ ዛሬ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የቅርጫት ኳስ ሜዳ በመገኘት የስፖርት ትጠቅና የኳስ ድጋፍ አድርጓል፡፡ በርክክብ ስነስርዓት ወቅት የተገኙት የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ይመር ኃይሌ እንደገለፁት ድጋፉ የተገኘው የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ስፔን ባርሴሎና ካለው  የአሴዴ ጋቫ የቅርጫት ኳስ ክለብና ከኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ጋር ባደረገው ግንኙነት ነው ፡፡ 430 ሺህ ብር የሚገመተው ይኸው ድጋፍ ፌዴሬሽኑ በክልሎች ላይ የቅርጫት ኳስ ስፖርትን ለማጠናከር የሚያደርገውን ጥረት የሚያግዝ ነው። ድጋፉ ከሀዋሳ ከተማ ስፖርት ክለብ ባሻገር ትምህርት ቤቶች ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑን አቶ ይመር ገልፀው "ይህም ትምህርት ቤቶች ለስፖርቱ መሰረታዊ እድገት ጉልህ ሚና ያላቸው በመሆኑ ነው "ብለዋል፡፡ ከቁሳቁስ ድጋፉ ባሻገርም ለአሰልጣኞች በአሴዴ ጋቫ ክለብ የስፖርት ባለሙያዎች አማካኝነት ሥልጠና እየተሰጠ መሆኑን አስረድተዋል። የአሴዴ ጋቫ ቅርጫት ኳስ ክለብ ፕሬዚዳንት ሚስተር ጃቪ ስቲቨን በበኩላቸው ሀዋሳ የባርሴሎና እህት ከተማ በመሆኗ እንደ ሁለተኛ ከተማቸው እንደሚቆጥሩዋት ተናግረዋል፡፡ ለድጋፉ መሳካት የከተማ አስተዳደሩና ፌዴሬሽኑ ጉልህ አስተዋፅኦ ማበርከታቸውን የገለፁት ሚስተር ጃቪ የሀዋሳ ከተማን የቅርጫት ኳስ ስፖርት ለመደገፍ የሶስት ዓመት ፕሮጀክት መቅረፁን አስታውቀዋል፡፡ የዛሬው ድጋፍ የዚህ ፕሮጀክት አካል መሆኑን ገልፀው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል ። የሀዋሳ ከተማ ባህል ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ሁሴን ከድር የሀዋሳ እህት ከተማ በሆነችው ባርሴሎና የሚገኘው የአሴዴ ጋቫ ቅርጫት ኳስ ክለብና ፌዴሬሽኑ ላደረጉት ድጋፍና ትብብር አመስግነዋል ። በከተማው ውስጥ ስፖርቱን ለማሳደግና ይበልጥ ተወዳጅ ለማድረግ የሚያበረክተው አስተዋፅኦ ከፍተኛ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ የሀዋሳ ከተማ ስፖርት ክለብ ካለው የቅርጫት ኳስ ቡድን በተጨማሪ በስሩ በርካታ ፕጀክቶችን በማቀፍ የማሳደግ ሥራ እየተሰራ መሆኑን በመጥቀስ ከቁሳቁስ ባሻገር ሙያዊ ስልጠናዎች ላይ በማተኮር ብቁ ተተኪዎችን ለማፍራት የሚያግዝ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ ከሀዋሳ ስፖርት ክለብ በተጨማሪ 12 የትምህርት ቤት ፕሮጀክቶች ድጋፍ የተደረገላቸው ሲሆን ከዛሬ ጀምሮ እስከ ሐምሌ 13 የሚቆይ የፕሮጀክቶች ውድድርና የአሰልጣኞች ሥልጠና እንደሚካሔድ ተገልጿል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም