ችግኝ በመትከል አካባቢና ሰላምን መጠበቅ ይገባል-የሰላም ሚኒስቴር

77
አዲስ አበባ ኢዜአ ሀምሌ 10/2011 ህብረተሰቡ ችግኝ በመትከል አካባቢውንና ሰላሙን ሊያስጠብቅ ይገባል አሉ የሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል። የሰላም ሚኒስቴር በክረምት ወቅት ለማከናወን የታቀደው የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር የመስሪያ ቤቱ የመጀመሪያ ምዕራፍ ነው ያለውን የሁለት ሺህ ችግኞች ተከላ በየካ ተራራ አከናውኗል። የሚኒስቴሩ አመራሮችና ሰራተኞች በሁለተኛው ምዕራፍ ከአምስት ሺህ በላይ ችግኞች የመትከል ዕቅድ እንዳላቸውም አስታውቀዋል። በችግኝ ተከላ መርሃ-ግብሩ ላይ የሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል፤ የችግኝ ተከላ የአየር ንብረትን ለመጠበቅ፣ አካባቢን ጽዱና ለጤና ተስማሚ ከማድረጉም በላይ ለአገር ሰላም መረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል። የአካባቢ ጥበቃ ስራ ከሰላም ጋር በጥብቅ የተቆራኘ በመሆኑ እንዲህ አይነቱ የአረንጓዴ ልማት እንቅስቃሴ ፋይዳ ያለው በመሆኑ ችግኞችን ከመትከል በዘለለ ጥብቅ ክትትል ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል። በአገር አቀፍ ደረጃ የታቀደው አራት ቢሊዮን ችግኝ የመትከል ውጥን ሲሳካ አገሪቱን በዓለም አቀፍ ደረጃ በማስተዋወቅ ረገድም ሆነ በአረንጓዴ ልማት ከፍተኛ አስተዋፆኦ እንደሚኖረውም ጭምር ነው የገለፁት። በችግኝ ተከላ መርሃ-ግብሩ ላይ የተሳተፉት የሰላም ሚኒስቴር ሰራተኞች በበኩላቸው ችግኝ መትከል ለነገ የሚባል ተግባር ባለመሆኑ በየቤታቸው እና አካባቢያቸው እየተከሉ መሆኑን ተናግረዋል። ህብረተሰቡ በየደጁ እና በየአካባቢው ዛፍ በመትከል የነገይቱ ኢትዮጵያ የበለፀገች እና ለዜጎቿም ምቹ እንድትሆን እንዲሰራም አስተያየት ሰጥተዋል። የኢትዮጵያ ደን ሽፋን በጭፍጨፋ፣ በቃጠሎና መሰል ምክንያቶች መመናመኑ ይገለጻል። ይህን ለማስተካከል በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በተጀመረው የክረምት ችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር በመላ አገሪቱ አራት ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል ታቅዷል። የአረንጓዴ ልማት ንቅናቄው ውጥን ሲሳካ የአገሪቱን የደን ሽፋን ለማሳደግ ጉልህ ሚና እንደሚኖረውም ተገልጿል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም