አራቱ ክልሎች በአንድ ቀን 291 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል አቅደዋል

96
አዲስ አበባ ኢዜአ ሀምሌ 10/2011 የአረንጓዴ አሻራ ዕቅድን ለማሳካት የኦሮሚያ፣ የአማራ፣ የትግራይና የደቡብ ክልሎች በአንድ ቀን 291 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል መዘጋጀታቸው ተገለጸ። በግንቦት ወር 2011 ዓ.ም አራት ቢሊዮን ችግኝ የመትከል መርሃ-ግብር በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ይፋ መደረጉ ይታወሳል። ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም በአንድ ቀን 200 ሚሊዮን ችግኝ የመትከል ዕቅድ የዚሁ መርሃ-ግብር አካል መሆኑም ይታወቃል። "አረንጓዴ አሻራ" በሚል መሪ ሀሳብ በአንድ ቀን 200 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል በተያዘው ዕቅድ አራቱ ክልሎች 291 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ማቀዳቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል። በአንድ ቀን 200 ሚሊዮን ለመትከል የታቀደ ቢሆንም አራቱ ክልሎች ከታቀደው በላይ ችግኝ ለመትከል ዝግጅታቸውን በማጠናቀቅ ላይ መሆናቸው ተገልጿል። የኦሮሚያ ክልል ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም 126 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ዝግጅት እያደረገ መሆኑንና ለዚህም ለችግኝ መትከያ 106 ቦታዎች እና 53 የሚጠበቁ ስፍራዎች መዘጋጀታቸው ተገልጿል። ምስራቅ ሸዋ፣ ኢሉባቡር፣ ጅማ፣ አርሲ እና ምዕራብ ሸዋ በክልሉ የተለዩ ችግኙ የሚተከልባቸው ዞኖች ናቸው። በአማራ ክልል 108 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል የታቀደ ሲሆን ለችግኝ ተከላው 64 የተለዩ ቦታዎች እና 40 የሚጠበቁ ስፍራዎች መዘጋጀታቸው በመግለጫው ተመልክቷል። ችግኞቹ በባህርዳር፣ ሰሜን ሸዋ(ጣርማበር)፣ ሰሜን ጎንደር፣ ማዕከላዊ ጎንደር(ሶስት ስፍራዎች)፣ ሰሜን ወሎ እና ደቡብ ወሎ(ተንታ) ዞኖች የሚተከሉ ይሆናል። በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል 48 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል የታቀደ ሲሆን በክልሉ ለሚተከለው ችግኝ ስድስት ቦታዎች እና 21 የሚጠበቁ ስፍራዎች ተዘጋጅተዋል። ጉራጌ፣ ሀዲያ፣ ሲዳማ እና አርባ ምንጭ ደግሞ ለችግኝ ተከላው የተለዩ ዞኖች ናቸው። በትግራይ ክልል ዘጠኝ ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል የታቀደ ሲሆን አምስት የሚጠበቁ ስፍራዎች ለችግኝ ተከላው መዘጋጀታቸው ታውቋል። ችግኞቹም በመቐለ፣ አድዋ፣ ሽሬ፣ አዲግራትና ማይጨው ዞኖች እንደሚተከሉ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የተገኘ መረጃ ያመለክታል። በአራት ቢሊዮን ችግኝ የመትከል መርሃ-ግብር እስካሁን ከ 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን በላይ ችግኝ መተከሉን የችግኝ ተከላው ብሔራዊ አስተባባሪ ኮሚቴ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም