አሜሪካ የማይናማር የጦር ኃይሎች ኤታማዦር ሹምን ጨምሮ በአራት የጦር መኮንኖች ላይ ማዕቀብ ጣለች

304

ኢዜአ ሀምሌ 10/2011አሜሪካ በሮሂንጊያ ማህበረሰብ ላይ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ ላይ እጃቸው አለበት ያለቻቸውን የማይናማር የጦር ኃይሎች ኤታ ማዦር ሹም ሚን አውንግ ህላይን እና በሌሎች ሶስት ወታደራዊ መሪዎች ላይ ማዕቀብ መጣሏን አስታውቃለች።

በወታደራዊ መሪዎች ላይ የማዕቀብ እርምጃ የተወሰደው ከሁለት ዓመት በፊት 740 ሺህ የሮሂንግያ ማህብረሰብን ለስደትና ሌሎችን ለሞት በዳረገው የዘር ማጥፋት ወንጀል እጃቸው እንዳለበት አሳማኝ መረጃ ስለተገኘ መሆኑን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል።

ሚኒስትሩ ማይክ ፖምፒዮ እንዳሉት በማይናማር ወታደራዊ መኮንኖች ላይ ይፋዊ እርምጃ በመውሰድ አሜሪካ የመጀመሪያዋ ሀገር ናት።

የማይናማር መንግስት በሮሂንጊያዎች ላይ በተፈጸመው ጥቃት የተሳተፉ አካላት ላይ እርምጃ አለመውሰዱና አሁን ሰብዓዊ የመብት ረገጣዎች መቀጠላቸው እንደሚያሳስባቸውም ፖምፒዮ በመግለጫቸው ጠቅሰዋል።

በማዕቀቡ ከኤታ ማዦር ሹሙ በተጨማሪ እርምጃ የተወሰደባቸው ምክትል ኤታ ማዦር ሶኤ ዊን፣ ብር ጋዴር ጀኔራል ታን ኦ እና ብርጋዴር ጀኔራል አውንግ አውንግ እና የአራቱም ቤተሰቦች ላይ ነው።

ተንታኞች አሜሪካ የጉዞ ክልከላና ሌሎች ማዕቀቦችን በማይናማር ወታደራዊ መኮንኖች ላይ መጣሏ በዓለም አቀፍ ደረጃ በጦር ወንጀለኛነት ለመክሰስም በር ከፋች ነው ብለዋል።
ምንጭ፡-አል ጄዚራ