በጀታችንን በጨረፍታ

149
በሰውነት ጀምበሩ (ኢዜአ) አገራዊ በጀት የአንድ መንግሥት ዕቅድ የገንዘብ ተመን ነው። በዚህ በጀት አገራት በአመት ውስጥ ሊያከናውኗቸው ያሰቡትን ተግባራት ሁሉ የበጀት አፈጻጸምና ድልድል መመሪያ በማውጣት ይሰራሉ። በመሆኑም በኢትዮጵያ እንደ አገር ከንጉሰ ነገስቱ ዘመነ መንግስት ጀምሮ ነሐሴ 21 ቀን 1951 ዓ.ም. በተወሰነው ልዩ ህግ መሰረት በአዋጅ ቁጥር 162/1951 ከሐምሌ አንድ ቀን ጀምሮ የበጀት ቆጠራ እንደተጀመረ የታሪክ መዛግብት ያስረዳል። በዚህ ሕግ መሠረት የበጀት ዓመት ካሌንደር ተለይቶ ከሐምሌ 1 ቀን ጀምሮ እስከሚቀጥለው ዓመት ሰኔ 30 ቀን ድረስ ያለው የአንድ ዓመት የበጀት ዓመት ተብሎ መሰራት ተጀመረ። አገሪቷ ለበርካታ አመታት የየአመቱን የበጀት ዕቅድ በማውጣት ስትሰራ በመቆየቷ የባለፈው 2011 ዓ.ም. ሰኔ 30 የተጠናቀቀው የበጀት ዓመት 59ኛው ሲሆን ከሐምሌ 1 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ የሚቆየው በጀት አመት ደግሞ 60ኛው የአገሪቱ የበጀት ዓመት ተደርጎ ይወሰዳል። በዚህ መሰረት በ2012 ዓ.ም. የአገሪቷን ሁለንተናዊ ፍላጎቷንና የተጀመረውን ድህነትን የመቀነስ ሥራ ይከወንበታል ተብሎ የታሰበው በጀት የፌዴራል መንግስት በጀት 386 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር እንዲሆን በምክር ቤቱ በሙሉ ድምጽ መጽደቁ ይታወሳል። ይህም ከ2011 በጀት አመት ጋር ሲነጻጸር የ6 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ጭማሬ እንዳለውም ያሳያል። ከዚህም ጠቅላላ አገራዊ በጀት ውስጥ ለመደበኛ ወጪዎች 109 ነጥብ 46 ቢሊዮን ብር ወይም 28 በመቶ፣ ለካፒታል ወጪዎች 130 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር 33 በመቶ፣ ለክልል መንግስታት የሚሰጥ ድጋፍ 140 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብርና 36 በመቶ እና ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ 6 ቢሊዮን ብር 1 ነጥብ 55 በመቶ በሆነ ክፍፍል ተደልድሏል። ይህ ከባለፈው አመት ጋር ሲነጻጸር ማለትም ለካፒታል 55 በመቶ እና ለመደበኛ ከተያዘው 45 በመቶ የተለየ እንደሚሆን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በበጀት ዓመቱ ማጠቃለያ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአብራሩበት ወቅት ገልጸዋል። በዚህም አገሪቷን ከድህነት ለማውጣት የታሰበ እንደሆነ ገልጸው፤ ከአፍሪካ የሩዋንዳን አገር ለካፒታል 45 በመቶ በመመደብ ለድህነት ቅነሳ የምታደርገውን አሰራር ለማሳያነት አቅርበዋል። አገራዊ በጀቱ ባለፈው ዓመት ቅድሚያ ከተሰጣቸው የሰው ሀይል እና የመሰረተ ልማት  ግምባታ በተጨማሪ በምግብ ዋስትነና የወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ እንዲሁም የመስኖ ልማትና ግድብ ስራዎችን ያማከለ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ለምክር ቤት በአብራሩበት ወቅት አሳውቀዋል። በተለይ በዚህ በያዝነው በጀት አመት ለ3 ሚሊዮን ወጣቶች አዳዲስ የስራ ዕድል እንደሚፈጠር የገለጹት ደግሞ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የብሄራዊ ስራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ሰብሳቢ አቶ ደመቀ መኮንን ናቸው። በዚህም ከመካከለኛው ምስራቅ፣ የአውሮፓና ሩቅ ምስራቅ አገራት ጋር በተደረገ ስምምነት በ2012 በጀት አመት 50 ሺህ ስራ ፈላጊ ወጣቶችን በልዩ ልዩ የስራ ዘርፎች አሰልጥኖ ወደ ውጭ በመላክ የስራ አጥነት ቁጥሩን ለመቀነስ ድርድር እየተደረገ እንደሚገኝም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡ በተመሳሳይ በ2012 በጀት አመት ሊሰሩ በታቀዱ በሃገር ውስጥ ስራ ፈጠራ፣ በግብርና፣ በኢንዱስትሪዎች፣ በማዕድናትና  ልዩ ልዩ ፕሮጀክቶች ላይ ወጣቶች እንደሚሰማሩም ተገልጿል፡፡ የአገሪቱ የአመቱ በጀት ማለትም 289 ነጥብ 8 ቢሊዮን ከተለያዩ አገራዊ ገቢዎች የሚሟላ ሲሆን ሌላው 97 ነጥብ 1ቢሊዮን ጉድለቱን ከተለያዩ ብድሮች እንደሚሞላም ተገልጿል። ይህም ከባለፈው አመት በጀት ጉድለት 3 ነጥብ 6 በመቶ ጋር ሲነጻጸር የተጋነነ እንዳልሆነ እና አለም አቀፍ የበጀት ጉድለት ጣሪያን ያላለፈ እነደሆነ በመግለጽ የአገር ውስጥ ገቢን ማሳደግ እንደሚገባ ያሳሰቡት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ዶክተር እዮብ ተስፋዬ ናቸው። ምሁሩ  አክለውም ይህን 3 በመቶ የበጀት ጉድለት ከውጭ በተለያዩ አኳኋኖች እንደመጣ ወዲያውኑ ወደ ልማት ተኮር ስራዎች ካልተቀየረ ለግሽበቱ መናር ነዳጅ እንደመጨመር ይቆጠራል ብለው እንደሚያምኑም ተናግረዋል። ከዚህ ጋር በተየያዘ  በ2012 የተበጀተው አገራዊ በጀት ለዘመናት ታሞ የነበረውን አገራዊ ምጣኔ ሀብት እንዲያገግም ከማድረጉም በላይ የተጀመረውን አገራዊ ልማታዊ አካሄድ የሚደግፍ ነው ሲሉ የገለጹት የኢፌዴሪ ገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስትር ዴኤታ የሆኑት ዶክተር እዮብ ተካልኝ ናቸው። ሀላፊው አክለውም በዚህ በጀት አመት መንግስት ቅድሚያ ለሚሰጣቸው አገራዊ ፕሮጄክቶችና አገሪቷን ከድህነት ለማላቀቅ ብሎም ዜጎቹን የኑሮ ውድነትና ዘላቂ ልማት ላይ ያተኮረ ነው በማለት ገልጸዋል። በተያያዘ በባለፈው አንድ አመት ኢኮኖሚው ላይ የተተበተቡ ችግርችን በመፍታት አገሪቷ ያላትን የማደግ ፍላጎትና አቅም መጠቀም የሚያስችሉ የለውጥ አቅጣጫዎች መተግበራቸውን ገልጸው፤ ማሻሻያውም ከወዲሁ ፍሬ እያፈራ እንደሆነ አብራርተዋል። በዚህም  አገሪቷ ያላትን የቱሪስት መስዕብ እና የኢንቨስትመንት አማራጭ መስኮችን በመጠቀም መስራት በሚያስችል እና በርካታ ስራን በቀላሉ ለመከወን ዕንቅፋት የሆኑ በቁጥራቸው በርከት ያሉ ጠቋሚ ማነቆዎች መለየታቸውን ያስረዱት ደግሞ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አበበ አበባየሁ ናቸው። በዚህም የሀብትን ብክነት በመቀነስ የተያዘው በጀት በትክክል አላማ ላይ መዋሉን ማረጋገጥ እንደሚገባም ኮሚሽነሩ ተናግረዋል። በሌላ በኩል በዚህ አመት በበጀት አመቱ ትኩረት ከተሰጣቸው መካከል ደግሞ የክልሎች የበጀት ድጎማ ነው።  በባለፈው አመት 117 ቢሊዮን ብር በላይ የነበረ ሲሆን በዚህ አመት ግን ከ140 ቢሊዮን ብር ለድጎማ መያዙ በክልሎች ለሚነሳው ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል እና  ዕኩል ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ  የሚያግዝ እንደሆነ በረቂቅ በጀቱ  የተወያዩ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ሀሳባቸውን አንስተዋል። አባላቱ በማከልም  ለዘመናት ጥያቄ የነበረውን ዕኩል የመልማትና የማደግ ጥያቄን ይመልሳል ብለው እንደሚያምኑም አብራርተዋል። በአንጻሩ ግን በጀቱ ለክልሎች የሚከፋፈልበትአሰራር ትኩረት እንደሚያስፈልገውም ተከራክረዋል። ይህም በዚህ አመት ተግባራዊ ሊሆን የታሰበው የበጀት ድልድል ኮሚሽን በምክር ቤት ቀርቦ ሳይጸድቅ በጀቱ መጽደቁ እንደሚያሳስባቸውም ተናግረዋል። ይህን ችግር ለመፍታት ከአንድ ዓመት በፊት የበጀት ድልድሉን ፍትሃዊነት የሚያጣራና ምላሽ የሚሰጥ የጥናት ቡድን ተቋቁሞ እንደነበር ይታወቃል።  የፌዴሬሽን ምክር ቤት የጀመረው የበጀት ቀመር ማሻሻያ ስራ ሳይጠናቀቅና ለአሁኑ በጀት እንደ ግብዓት ሳይሆን መሰራቱ አሁንም “የፍትሃዊነት ጥያቄ አያስናሳም ወይ” የሚል ጥያቄ አባላቱ አቅርበዋል። ይህ አካሄድ አንደኛ  በክልሎች ለሚካሄዱ የመሰረተ ልማት ስራዎች ትክክለኛ መስፈርት ባለመኖሩ ለፍታዊነት መጓደል መንስኤ ሊሆን እንደሚችልም የምክር ቤት አባላት ሀሳባቸውን ሰንዝረዋል። በዚህም በኢፌዴሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 41(3) ላይ እንደተገለጸው ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ በመንግሥት ገንዘብ ከሚካሔዱት ማኅበራዊ አገልግሎቶች እኩል የመጠቀም መብት አለው ብሎ የሚደነግገውን የሚጣረስ እንደሆነ የዘርፉ ምሁራን ያስረዳሉ። ሌላው መንግሥት ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታው እንዲሻሻልና እኩል ዕድል እንዲኖረው ሀብትን በፍትሐዊነት የማከፋፈል ግዴታ እንዳለበት በአንቀጽ 89(2) የተቀመጠው መንግሥታዊ ግዴታ ነው፡፡ ሌላው በዚሁ አንቀጽ ላይ የተገለጸው እና ሶስተኛው መርህ ደግሞ በዕድገት ወደኋላ ለቀሩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ልዩ ድጋፍ የማድረግ የፌዴራል መንግሥት ግዴታ ነው የሚል ነው፡፡ አራተኛው ደግሞ የፌደራል መንግሥትም የራሱን፣ ክልልም የራሱን ወጪ የመሸፈን መርሕ ሲሆን ምንጩም አንቀጽ 94(1) ነው፡፡ የመጨረሻው፣ የተመጣጠነ ዕድገትን በማያፋልስ ሁኔታ ለክልሎች ድጋፍ የማድረግ መርሕ የሚለው በአንቀጽ 94(2) ላይ የተቀመጠው ድንጋጌ ነው፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግስት ለክልሎች የበጀት ድጎማ የሚያደርግበት ሁለት መሠረታዊ ምክንያቶች አሉት። የመጀመሪያው ምክንያት የክልሎች መንግስታት ያላቸውን የተፈጥሮ፤ የሰው ሃይልና ካፒታል ሃብቶችን በአግባቡ ማደራጀት ባለመቻላቸው የተነሳ፣ አስተዳደራዊ ወጫቸውን መሸፈን ባለመቻላቸው ምክንያት ሲሆን ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ መንግስት በሁሉም ክልሎች እኩል የሆነ የኢኮኖሚ እድገት ማምጣት ሃላፊነት ስላለበት እንደሆነ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ያስረዳሉ። በመሆኑም መንግስት በሁለተኛው ምክንያት የተነሳ እኩል ያልሆነ የሃብት ክፍፍል ፖሊሲ በመንደፍ በክልሎች መኃል እኩልነት መፍጠር የሚያስችል አካሄድ መንደፍ እንደሚገባም ምሁራኑ ያስረዳሉ። ሌላው ለክልሎች ለሚደረገው የበጀት ድጎማ በህዝብ ቁጥራቸውና በልማት ወደኋላ ለቀሩ ክልሎች በመቶኛ መብለጥ የሚል ነው። ይህ ደግሞ ምንም አይነት ወቅታዊ የህዝብ ቁጥር መረጃ ሳይኖር ይህን የበጀት የድልድል ቀመር ተግባራዊ ማድረጉ አሁንም የፍትሀዊነት ጥያቄ ያመጣል ብለው እንደሚያምኑም የምክር ቤቱ አባላት ተሟግተዋል። በኢትዮጵያ በጀት ድልድል ታሪክ መሰረት ደግሞ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚለዋወጥ እንደሆነ ያሳየናል(።  ለዚህ ማረጋገጫው በ1987ዓም የበጀት ዓመት የበጀት ድልድል በመቶኛ የሚታሰብ እንደነበር ያስረዳናል። በዚህም የክልሎቹ ለሕዝብ ብዛት 30፣ ከማዕከል ለሚኖር ርቀት 25፣ ገቢ ለማመንጨት አቅም 20፣ ከዓመት በፊት ለልማት ለተመደበው የበጀት ዓመት 15፣ እና ለክልሉ የቆዳ ስፋት 10 ነጥቦች ተሰጥተውት እንደነበር ከፌዴሬሽን ምክር ቤት የተገኘ መረጃ ያሳያል። በሌላ በኩል ደግሞ በ1988 የበጀት ዓመት ከላይ የነበሩት መመዘኛዎች  ቀርተው ሦስት ነገሮችን በመውሰድ እኩል 33.3 ከመቶ ነጥብ ተሰጣቸው፡፡ እነዚህም የሕዝብ ብዛት፣ ክልሉ ያለበት የዕድገት ደረጃና በ1987 የበጀት ዓመት የሰበሰቡት የገቢ መጠን በሚል። አሁንም በሌላኛው አመት ሌላ መመዘኛ ይዞ ብቅ ብሎ እንደነበር በማውሳት አብዛኛውን ፐርሰንት ለህዝብ ቁጥር በመስጠት ሌላኛውን ደግሞ በልማት ላሉበት ደረጃ እንደነበር ይታወቃል። እሱም በተከታታይ በመቶኛ 60 እና 25 እንደነበር መረጃው ያሳያል። አሁን ሌላኛው ችግር ደግሞ የትኛውም ክልል በየትኛውም መስፈርትና መመዘኛ የሚያገኘው በጀትን የፌዴራል መስተዳደር በጀቱን ምን ላይ እንዳዋሉት የመከታተያ እና ኦዲት የማድረጊያ መዋቀራዊ አሰራር አለመኖሩ ነው። ለዚህም ማሳያው በአንድ ወቅት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ‹‹ማረሻ እንዲገዙበት ብንሰጣቸው ለገንፎ አዋሉት›› በማለት የሚጠይቁበት አሰራር አለመኑሩን በስላቅ መግለጻቸው የሚታወስ ነው። እናም ለዚህ ሁሉ ችግር መፍቻ ቁልፍ ይሆን ዘንድ ተስፋ የተጣለበትን በጥናት ላይ የተመሰረተ ፍትሃዊ የክልሎች የበጀት ቀመር ድልድልን ተፈጻሚ ለማድረግ የሚያግዘው  ኮሚሽን ሳይቋቋም በጀቱ መጽደቁ ለበርካቶች ጥያቄ ሊፈጥር ይችላል። ከዚህ በፊት በመተሳሳብ ሲደረግ የነበረው ድልድል ተደጋጋሚ የበጀት እና የተጨማሪ የገንዘብ ድጎማ ጥያቄዎች ከተለያዩ ክልሎች ሲቀርብ እንደነበረና  ይህም  በፍትሃዊነት ላይ ችግር እንዳለበት ሲተች እንደቆየ  የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም ገልጸዋል።  በፌዴሬሽን ምክር ቤት የገቢ ክፍፍል ጥናት ከፍተኛ ባለሙያ ዶክተር ዘውዱ ከበደ  በበኩላቸው ኮሚሽኑ ያስፈለገው ለክልሎች የሚደለደለውን የበጀት ድልድል ቀመር ህግና ስርዓት የተከተለ እንዲሆን ለማስቻል እንደሆነም አስረድተዋል። ረቂቅ የሕግ ማዕቀፉ የፌዴራል መንግሥት ለክልሎች ስለሚሰጠው የድጎማ ዓይነትና ክፍፍሉ የሚፈጸምባቸውን መርሆች አስመልክቶ ከያዛቸው ድንጋጌዎች በተጨማሪ፣ ክልሎችና የፌዴራል መንግሥት የጋራ ገቢዎቻቸውን የሚከፋፈሉበትን መርህና ሥርዓት የተመለከቱ ድንጋጌዎችንም አካቷል። በጥቅሉ ወደ ክልል የሚላኩ የድጎማ ገንዘብ ከላይ ከቀረበው መረጃ እንደምንረዳው አንዳንድ ክልሎችን የበለጠ እንደሚጠቅም ቢታሰብም፣ ውጤታማ የሆነ አጠቃቀምና አያያዝ አሁንም የጎደለው መሆኑን ሌሎች ክልሎችን የሚጎዳ መሆኑን ነው። ሌሎች ክልሎች ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ በመጥፎ ትምህርትነትም እኩል ተጠያቂነት እንዳይኖር ከማድረግ አንፃርም አድልኦ ስለሚሆን ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ካልሆነ የሚሰጠው ድጎማ ላይ ሌሎች ክልሎች በተቃራኒው ድምፅ ቢሰጡ ችግሩ የባሰ ሊሆን ይችላልና  የሚታየውን ረጅም ብሮክራሲ በመቀነስ እና ለሙስና አጋላጭ የሆኑ አሰራሮችንና አካሄዶችን በማስወገድ  በጀቱ በትክክል ለታለመለት አላማ እንዲውል እና አገሪቷ ለዜጎቿ ሙሉ ፍላጎትን የምታሟላ እንድትሆን በትብብር መስራት ይገባል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም