በክረምቱ የሚካሄደው ችግኝ ተከላ አንድነትን ለማጎልበት ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ተገለጸ

76
አዲስ አበባ ኢዜአ ሀምሌ 9/2011 ከዘጠኙም ክልሎችና ከሁለቱም ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ ከ350 የሚበልጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ዛሬ በአዲስ አበባ ከተማ ችግኝ ተክለዋል። በክረምት በጎ አድራጎት ከዘጠኙም ክልሎችና ከሁለቱም ከተማ አስተዳድሮች የተውጣጡ የሃይማኖት አባቶች፣ የጎሳ መሪዎች፣ ወጣቶችና አመራሮችን ጨምሮ ከ350 በላይ የሆነ የህብረተሰብ ክፍል በችግኝ ተከላው ተሳትፈውበታል። ችግኝ ተከላውም በአዲስ አበባ ከንቲባ ቢሮ ተጀምሮ መዳረሻውን አፍሪካ ፓርክ አድርጓል። በእለቱም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ "አዲስ አበባ የሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች ከተማ" በመሆኗ በአንድነት መዲናዋን አረንጓዴና ውብ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል። መርሃ ግብሩ ከችግኝ ተከላው ባሻገር የአንድነትን ስሜት እንደሚፈጥርም ተናግረዋል። ከሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች የመጡ ዜጎች የተከሉት ችግኝ ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ የሚያስገኘውን ጥቅም በማስረዳት ችግኙን የመንከባከቡ ሃላፊነት ለነዋሪዎች ይተላለፋል። የከተማዋ ነዋሪዎች ችግኞቹን በመንከባከብና በመጠበቅ ድርሻቸውን እንዲወጡ መልእክታቸውን ያስተላለፉት በአዲስ አበባ ከተማ የባህል ቱሪዝምና ኪነጥበባት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ገብረመስቀል ካሳ ናቸው። አያይዘውም በዚህ ተግባር በዋናነት ሊተላለፍ የተፈለገው መልዕክት "መዲናዋ የሁሉም ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች" በመሆኗ ለከተማዋ ጽዳትና ሰላም ሁሉም 'የኔነት' ስሜት ተሰምቶት የድርሻውን እንዲያበረክት ነው ብለዋል። የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ሃምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም የሚከናወነው 200 ሚሊዮን ችግኝ የመትከል‘የዜጎች የአረንጓዴ አሻራ ቀን’ ምቹ አየር ከመፍጠር ባሻገር አገሪቱን በበጎ ጎን እንድትታወቅ ያደርጋል። ተግባሩ የአገሪቱ ዜጎች ተቀራርበው እየጠፋ ያለውን የአብሮነት እሴት መልሶ በመገንባት፣ አገርን በደቦ የማሳደግ ባህል በማዳበር፣ በሰላምና በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የባለቤትነት ስሜት ለመፍጠር የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል። ብዝሃነት የልዩነት ምክንያት ሳይሆን የውበትና የብዙ ችግር መፍቻ ቁልፍ ተደርጎ መታየት እንዳለበትም አሳስበዋል። ንቅናቄው በአገሪቱ ባህል ለጥንካሬ ምሳሌ የሆነውን የወይራ ዛፍ በአዲስ አበባ ከንቲባ ቢሮ በመትከል መጀመሩን ዶክተር ሂሩት ገልጸዋል። ከአማራ ክልል ደላንታ ወረዳ የመጡት አቶ ፍሰሃ በላይ በመዲናዋ በጋራ ሆኖ ችግኝ መትከል የአንድነት ስሜት መፍጠሩንና መዲናዋ የሁሉም ኢትዮጵያዊ መሆኗን የሚገልጽ ስሜት መፍጠሩን ተናግረዋል። ከደቡብ ክልል ከአርባ ምንጭ የመጡት አለቃ መለቦ መንቻ ተሰባስቦ ችግኝ መትከል ተቀራርቦ ለመስራት እንደሚረዳና ልማቱን ለማስቀጠል እንደሚያግዝ ተናግረዋል። ከኦሮሚያ ክልል ለገጣፎ የመጡት ወይዘሮ ሙሉመቤት ገመዳ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ በጎ ምግባሩ አብሮነትን ለመፍጠርና ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ወሳኝ ከመሆን ባለፈ አንድነትን ያጠናክራል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም