በሀገሪቱ በተያዘው የምርት ዘመን አስራ አራት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ለማልማት እየተሰራ ነው

65
አዳማ ኢዜአ ሐምሌ 9/2011 በሀገሪቱ በ2011/2012 የምርት ዘመን አስራ አራት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በተለያየ ሰብል ለማልማት እየተሰራ መሆኑን የግብርና ሚኒስትር አስታወቀ። የፌደራልና ክልሎች የግብርና ልማት አመራር አካላት የተሳተፉበት የጋር የምክክር መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተጀምሯል። በዚህ ወቅት የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ዑመር ሁሴን እንደገለጹት በተያዘው የምርት ዘመን የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ርብርብ እየተደረገ ነው። በምርት ዘመኑ  14 ሚሊዮን  ሄክታር መሬት በማልማት አራት መቶ አምስት ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማሰባሰብ ግብ  ተቀምጦ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል። ለዚህም ስኬታማነት  ቀደም ብሎ  የግብአት ዝግጅት በማድረግ  ስድስት ሚሊዮን 500ሺህ ለሚሆኑ የግብርና ባለሙያዎች ፣ አርሶና አርብቶ አደሮች ስልጠና መሰጠቱን ጠቅሰዋል። የተሰጠው ስልጠና በአቅም ግንባታና በተነሳሽነት ዙሪያ ያሉትን ማነቆዎች ለመፍታት እንደሚያግዝ ሚኒስትሩ  አስረድተዋል። ባለፈው የመኽር ወቅት የተገኙ መልካም ተሞክሮዎችን በማስፋት ለአሁኑ የምርት ወቅት  ለመጠቀም ጭምር ተመቻችቷል። "እስካሁን ያለውን  የዝናብ  ሁኔታ  ጥሩ ቢሆንም በቀጣይም ያለውን እጥረትና የበሽታ ክስተትን ለመቋቋም የሚያስችል ዝግጅትና ጥረት ያስፈልጋል" ብለዋል። እንደ ሚኒስትሩ ገለፃ በተያዘው የምርት ዘመን ለማልማት የታቀደው የእርሻ መሬት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጻር ብልጫ ይኖረዋል። ለሶስት ቀን በሚቆየው በዚሁ መድረክ  የሚኒስቴሩና  የሁሉም ክልሎች በዓመቱ የተካሄዱ የበልግና የመስኖ ፣ የእንሰሳት ልማትና መኽር አዝመራ እንቅስቃሴ  ሪፖርቶች ቀርበው  ውይይት እንደሚደረግባቸው ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም