ፓርቲው መንግስት ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ አገር የማረጋጋት ሃላፊነቱን እንዲወጣ ጠየቀ

59
አዲስ አበባ ኢዜአ ሀምሌ 9/2011 መንግስት ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ አገር የማረጋጋት ኃላፊነቱን እንዲወጣ የኢትዮጵያ ሰላማዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢሰዴፓ) ጥሪ አቀረበ። ፓርቲው ለኢዜአ በላከው መግለጫ አገራዊ ለውጡን የሚደግፉ እንዳሉ ሁሉ አገሪቱን ለመበታተን የሚንቀሳቁ እንዳሉ ገልጿል። አገራዊ ለውጡን እንደሚደግፍና በኢትዮጵያ አንድነት ላይ የማይደራደር መሆኑን የገለጸው ፓርቲው፤ በአገሪቱ ላይ የሚታየው አደጋ በጣም አስጊ በመሆኑ የኢትዮጵያ መንግስት ሃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት ጠይቋል። በትግራይና በአማራ ክልል እንዲሁም በደቡብ ክልል ሲዳማ አካባቢ የሚስተዋለውን ጉዳይ ለአብነት ያነሳው ፓርቲው፤ "ሰላማችን አንዴ ካመለጠ ልንቆጣጠረው የማንችለው አደጋ ነው" ብሏል በመግለጫው። በመሆኑም መንግስት በከፍተኛ ጥንቃቄ አገር የማረጋጋት ሃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርቧል። "አገራችን አደጋ ላይ ወድቃለች" ያለው መግለጫው፤ ህዝብን በመከፋፈል ወደ እሳት ለመክተት የሚራሯጡ ሃይሎችን የኢትዮጵያ ህዝብን ማውገዝ እንዳለበት ኢሰዴፓ በመግለጫው አሳስቧል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም