በደቡብ ክልል የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ባህልና የዘወትር ተግባር እየሆነ ነው

82
ሀዋሳ ኢዜአ ሐምሌ 9/2011  የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በወጣቱ ዘንድ ባህልና የዘወትር ተግባር እየሆነ መምጣቱን በሀዋሳ ከተማ ኢዜአ ያነጋገራቸው በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ገለጹ። በደቡብ ክልልከ2ሚሊዮን 800ሺህ በላይ ወጣቶች በ11 ዘርፎች የተለያዩ የበጎፈቃድ አገልግሎት እንዲሰጡ መመቻቸቱን የክልሉ ሴቶች፣ህጻናትናወጣቶች ቢሮ አስታውቋል። በሀዋሳ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ይሰጡ የነበሩ ወጣቶች እንዳሉት ቀደም ባሉት ዓመታት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የክረምት ስራ ብቻ አድርገው ይወስዱት ነበር። የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ወስዶ ውጤቱን እየተጠባበቀ እንደሚገኝ የገለጸው ወጣት አሸብር በላይ በሰጠው አስተያየት የመሰናዶ ተማሪ በነበረበት ወቅት ላለፉት ሁለት ክረምቶች በበጎ ፈቃደኞች ይሰጥ የነበረውን የማጠናከሪያ ትምህርት ይከታተል እንደነበር ተናግሯል። በዩኒቨርሲቲ በጎ ፈቃደኛ ተማሪዎች እገዛ ጥሩ ዝግጅት አድርጎ መፈተኑን ገልጾ እሱም በተራው ዘንድሮ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመሰማራቱ ደስተኛ መሆኑን አስረድቷል። በክረምቱ የእረፍት ወቅት በከተማ ጽዳት ፣ ለአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠት ፣ በችግኝ ተከላና በሌሎች መስኮች በመሰማራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ገልጿል። በዲላ ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ዓመት ተማሪዋ ወጣት ትዕግስት መኮንን በበኩሏ በበጋው ወቅት በትምህርት ላይ እያለችም በእረፍት ቀናት በደም ልገሳና ለጌዴኦ ተፈናቃዮች ድጋፍ የማሰባሰብ ስራ ስታከናውን መቆየቷን ተናግራለች። ቀደም ሲል የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በክረምት ወራት ብቻ የሚፈጸም ስራ ተደርጎ ይወሰድ እንደነበር አስታውሳ ይህ አመለካከት እየተቀየረና የዘወትር ተግባር እየሆነ መምጣቱን ጠቁማለች። "የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ባህል ሊሆን ይገባል" ያለችው ተማሪዋ ችግር ሲያጋጥም የክረምት የእረፍት ወቅት ላይ አልያም በአጋጣሚ ከማድረግ ባለፈ ሁሌም የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት ፣ ደም በመለገስና በአካባቢ ጥበቃ ተግባራት ላይ በመሳተፍ ህዝብን ማገልገል እንደሚገባ አመልክታለች። በሀዋሳ የመናኸሪያ ክፍለከተማ ነዋሪ እንደሆነ የሚናገረው ወጣት ደረጀ ደስታ አምና ቤታቸው የፈረሰባቸው አቅመደካሞችን ቤት የማደስ ስራ ላይ በመሳተፍ ለመጀመሪያ ጊዜ በበጎፈቃድ አገልግሎት ተሰማርቶ እንደነበር አስታውሷል። በዛን ወቅት ቤታቸው የታደሰላቸው አቅመ ደካሞች ያሳዩት ፍቅርና ምርቃት ያሳደረበት ስሜት ዘንድሮም የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራ ላይ ለመሰማራት እንዳነሳሳው ተናግሯል። በክረምቱ ወቅት እስከ 200 ችግኝ በመትከል በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተያዘውን 4 ቢሊዮን ችግኝ የመትከል ዕቅድ ለማሳካት የበኩሉን እንደሚወጣ ገልጿል። በዘንድሮው የክረምት ወራት በደቡብ ክልል በትምህርት ፣ በጤና ፣ በከተማ ጽዳትና ውበት ፣ በግብርናና የአካባቢ ጥበቃን ጨምሮ በ11 ዘርፎች የተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራዎች እንደሚከናወኑ የክልሉ ሴቶች ፣ ህጻናትና ወጣቶች ቢሮ አስታውቋል። በቢሮው የወጣቶች ማካተት ተሳትፎና ንቅናቄ ዳይሬክተር አቶ በረከት በርገና እንዳሉት ከ2ሚሊዮን 800ሺህ በላይ ወጣቶች የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራ ላይ እንደሚሳተፉ ይጠበቃል ። በክልሉ 18 ዞኖችና 7 ልዩ ወረዳዎች በሚከናወኑ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች  2ቢሊዮን 500 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው ስራዎች በማከናወን ከ 2 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዷል ። አምና በክልሉ ውስጥ ከነበረው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በተጨማሪ 250 ወጣቶች ክልሉን ወክለው ወደ ሌሎች አካባቢዎች መሰማራታቸውንና 150 ወጣቶች ደግሞ ከተለያዩ ክልሎች ወደ ደቡብ መጥተው አገልግሎት መስጠታቸውን ዳይሬክተሩ አስታውሰዋል ። በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ተከስቶ በነበረው ችግርና ከኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞኖች የተፈናቀሉ የህብረተሰብ ክፍሎች በተጠለሉባቸው ጣቢያዎች በመገኘት ወጣቶቹ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መስጠታቸውንም አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም