የኢትዮጵያ ቆዳና ሌጦ የስብ ይዘት አነስተኛ ስለሆነ ብዙ የማበልጸጊያ ኬሚካል መጠቀም እንደማያስፈልግ ተገለጸ

1117

አዲስ አበባ ኢዜአ ሀምሌ 9/2011 የኢትዮጵያ ቆዳና ሌጦ የስብ ይዘት አነስተኛ ስለሆነ ፋብሪካዎች ብዙ የማበልጸጊያ ኬሚካል መጠቀም እንደማያስፈልጋቸው አንድ ጥናት አመለተ።

የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢኒስቲትዩት በአገሪቷ በቆዳና ሌጦ ዘርፍ ያሉ ችግሮችን አስመልክቶ በኬሚካል አጠቃቀም፣ ስነ- ባህሪና ተጽእኖን መቀነስ በሚቻልበት ማሻሻያ ስልት ላይ ያካሔደውን ጥናት ይፋ አድርጓል።

ጥናቱ ላለፉት ሶስት ዓመታት በ37 የእንስሳት የቆዳ ዝርያዎች ላይ የተካሄደ ሲሆን ፤ ከነዚህ መካከል 12ቱ በከብት ፣ 15ቱ በበግና አስሩ ደግሞ በፍየል ላይ የተደረገ ነው።

የጥናቱ አቅራቢ አቶ መሃመድ ሁሴን እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ቆዳን በማልማትና የቆዳ ውጤቶችን በማምረት ረገድ ቀደምት ከሆኑ አገሮች መካከል አንዷ ናት።

ኢትዮጵያ በተለይም በአለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የቀንድ ከብት ሃብት ያላት መሆኑዋን አስታውሰው፤ ይህም ቆዳና የቆዳ ውጤቶችን ለዓለም አቀፍ ገበያ በማቅረብ የውጪ ምንዛሪ ለማስገኝት እንዲሁም በአገር ውስጥ ጥቅም ላይ ለማዋል ከፍተኛ አቅም መሆኑን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ የቆዳና ሌጦ ይዘት ከህንድ እና ከመሳሰሉት ሌሎች አለም አገሮች ጋር ሲነጻጸር የተሻለ መሆኑን ነው በዚሁ ወቅት የተገለፀው።

ይሁንና የአገሪቷ የቆዳና ሌጦ የስብ ይዘት በአማካይ ከ3 እስከ 13 በመቶ ሲሆን፤ ይህም የሚያመላክተው የስብ ይዘቱ ዝቅተኛ መሆኑን ነው።

የኢትዮጵያ ቆዳና ሌጦ የስብ ይዘት አነስተኛ መሆን ፋብሪካዎች የሚጠቀሙት ከፍተኛ የማበልጸጊያ ኬሚካል አላስፈላጊ ብክነት እንዳስከተለ ጥናቱ ጠቁሟል።

በመሆኑም በአገር ውስጥ የሚመረተው ቆዳ የጥራት ጉድለት እንዳይከሰትበትና በአለም አቀፍ ገበያ ላይ ተወዳዳሪ እንዲሆን ጥቅም ላይ የሚውለውን የማበልጸጊያ ኬሚካል መጠን መቀነስ እንደሚገባ ነው ጥናቱ ያመለከተው።

በሌላ በኩል እንስሳቶቹ የሚውሉበት አካባቢ እንደ እከክ፣ እሾህና የመሳሰሉ በሽታዎች ተጠቂ በመሆናቸው የቆዳ ጥራቱ እንዲቀንስ ዋነኛ ምክንያት መሆኑንም አብራርተዋል።

ይህም የሚመረቱ የቆዳ ውጤቶችን እሴት ጨምሮ ወደ ውጪ አገሮች ለመላክና በዘርፉ ተወዳዳሪ ለመሆን በሚደረጉ ጥረቶች ላይ እንቅፋት እንደሚሆን ነው የገለጹት።

የቆዳ ጥራቱን ጨምሮ ወደ ውጭ የሚላኩ ውጤቶችን ከፍ በማድረግ ተጠቃሚ መሆን እንዲቻል በተለይም በተበከሉ ውሃዎች ሳቢያም እንስሳት ተጠቂ እንዳይሆኑ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

እንዲሁም ከውጭ አገሮች ጋር በመቀናጀት አስፈላጊ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀምና ፋብሪካዎችም ማጣሪያዎችን መገንባት እንደሚገባቸውም በጥናቱ ተብራርቷል።