በትግራይ 442 ሺህ ሔክታር መሬት በዘር ተሸፈነ

73
መቀሌ ኢዜአ ሀምሌ 9/2011 በትግራይ ክልል በዘንድሮ የመኽር አዝመራ እስከ አሁን ድረስ 442 ሺህ ሔክታር መሬት ታርሶ በዘር መሸፈኑን የክልሉ ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ አስታወቀ። በቢሮው የአዝርዕት ልማት አስተባባሪ አቶ ኃይሌ አባይ እንዳሉት ታርሶ በዘር የተሸፈነው በምርት ዘመኑ ለማልማት ከታቀደው አንድ ሚሊዮን 200ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ ነው። ማሽላ፣ ዳጉሳ፣ በቆሎ፣ ስንዴ፣ ገብስና ሌሎችም የሰብል ዓይነቶች አስፈላጊው ግብአት በመጠቀም በመስመር እንዲዘሩ ተደርጓል ። የክልሉ አርሶ አደሮች በኩታገጠም ተደራጅተው በገበያ ተፈላጊ ለሆኑት ሰብሎች ልዩ ትኩረት ሰጥተው እያለሙ መሆናቸውን አስተባባሪው ተናግረዋል ። ለምርቱ ተገቢውን ገበያና ዋጋ እንዲያገኝ ለማድረግ ከወዲሁ ከህብረት ስራ ማህበራት ጋር የሚያስተሳስር አደረጃጀት መፈጠሩንም አመልክተዋ። አርሶ አደሮቹ በዘር ለሸፈኑት መሬት 99 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያና 5 ሺህ 359 ኩንታል ምርጥ ዘር ተጠቅመዋል ። በልማቱ ከተሰማሩ አርሶ አደሮች መካከል በማዕከላዊ ዞን ዓድዋ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ተስፋሚካኤል ትኩዕ በሰጡት አስተያየት በበጋ ወራት ያከናወኑት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በመኽር አዝመራ ወቅተ ጥቅሙ ጎልቶ እየታየ መሆኑን ተናግረዋል ። በሁለት ሄክታር ማሳ ላይ ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ ተጠቅመው ዳጉሳና ስንዴ መዝራታቸውን አመልክተው ጤፍ ለመዝራትም መሬታቸው ደጋግመው በማረስ ማለስለሳቸውን አስረድተዋል። በሁለት ሔክታር መሬታቸው ላይ  ለቀለብና ለገበያ የሚሆኑ ሰብሎችን መርጠው በመዝራት ላይ እንደሆኑ የተናገሩት ደግሞ በእንደርታ ወረዳ የአይናለም ቀበሌ አርሶ አደር መሀሪ ገብረእግዚአብሔር ናቸው። በደጋተምቤን የሩባ ወይኒ ቀበሌ ሴት አርሶ አደር ለምለም ገብረኪዳን በበኩላቸው በሁለት ጥማድ ማሳቸው ላይ  ማሽላ መዝራታቸውን ገልጸዋል ማሳቸውን በጤፍ ለመሸፈን ደግሞ ከኩታ ገጠም አርሶ አደሮች ጋር ተደራጅተው እየሰሩ መሆናቸውን ገልፀው እያንዳንዷን የዝናብ ጠብታ ለአዝመራው ጥቅም ለማዋል እየሰሩ መሆናቸውን አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም