የደሴው ንጉስ ሚካኤል ትምህርት ቤት በ100 ሚሊዮን ብር ዘመናዊ ግንባታ ሊካሔድለት ነው

112
ደሴ ኢዜአ ሐምሌ 9/2011 ከ90 ዓመት በላይ እድሜ ያለው የደሴው ንጉስ ሚካኤል ትምህርት ቤት በ100 ሚሊዮን ብር ወጪ በዘመናዊ መንገድ ለመገንባት የሚያስችል የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠለት። የመሰረት ድንጋዩ የተቀመጠው ትናንት የትምህርት ቤቱ 90ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በተከበረበት ወቅት ነው ። የደሴ ንጉስ ሚካኤል ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ገብሩ ወንድሙ እንደገለጹት ትምርት ቤቱ ዕድሜ ጠገብ ቢሆንም እስከ አሁን ድረስ ዘመናዊ ቤተ መጽሀፍት፣  ቤተ ሙከራ፣ ምቹ የመማሪያ ክፍልና የአስተዳደር ህንጻ አልነበረውም፡፡ ላለፉት 90 ዓመታት ጥገና ተደርጎለት እንደማያውቅም አመልክተዋል። እስከ አስረኛ  ክፍል ድረስ ያስተምር የነበረው የንጉስ ሚካኤል ትምህርት ቤት የመሰናዶ ትምህርት ጭምር እንዲያካትት ተደርጎ በ100 ሚሊዮን ብር የሰባት ህንፃዎች ግንባታ ይደረግለታል። ትምህርት ቤቱን ዘመናዊነት ለማላበስ የተያዘውን አቅድ ለማሳካት ህብረተሰቡ ከወዲሁ 8 ሚሊዮን ብር ማዋጣቱን ከርዕሰ መምህሩ ገለፃ ለማወቅ ተችሏል ። 250 ሺህ ብር ዋጋ እንደሚያወጣ የተገመተው የግንባታው ዲዛይን በነፃ ሰርተው ያስረከቡት ኢንጅነር አሊ ሰይድ  በሰጡት አስተያየት "እስከ ግንባታው ፍፃሜ ድረስ ሙያዊ እገዛ ለማድረግ ዝግጁ ነኝ "ብለዋል ። የደሴ ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ አሸናፊ አለማየሁ በበኩላቸው ህብረተሰቡ የመንግስትን እጅ ሳይጠበቅ በራሱ ተነሳሽነት የሚያደርገው የማስፋፊያ ግንባታ የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል። መንግስት በሁሉም ቦታ መድረስ ስለማይችል የንጉስ ሚካኤል ትምህርት ቤት ተሞክሮ በማስፋት ሌሎች ትምህርት ቤቶችም ምቹ የመማር ማስተማር ሁኔታ በመፍጠር ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ እንደሚደረግ ገልጸዋል። የንጉስ ሚካኤል ትምህርት ቤት በወሎ የመጀመሪያው ዘመናዊ ትምህርት የተጀመረበት ቢሆንም ትኩረት በማጣቱ ምክንያት ወደ ኋላ የቀረና የመፍረስ አደጋ ተጋርጦበታል፡፡ አቶ አሸናፊ እንዳሉት  የጥንት ይዘቱን ጠብቆ እንደ ቅርስነት ጭምር እንዲያገለግልም ከወሎ ዩኒቨርሲቲ ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው። የደሴ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ መላኩ ሚካኤል እንደገለፁት የትምህርት ቤቱ እቅድ ተግባራዊ እንዲሆን የከተማ አስተዳደሩ ድጋፍና ክትትል በማድረግ ሃላፊነቱን ይወጣል። የትምህርት ቤቱ ግንባታ በመጪው መስከረም ወር እንደሚጀመርና የሚያልቀው ግን ህዝቡ በሚበረከተው የገንዘብ ድጋፍ ይወሰናል ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም