“ትራምፕ ዓይን ያወጣ የዘረኝነት ጥቃት ፈፅመዋል”- ኤልሃን ኦማር

132
ሐምሌ 9/2011 ትውልደ ሶማሊያዊቷ የአሜሪካ የህግ አውጭ ምክር ቤት አባል ኤልሃን  ኦማር “ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በይፋ የዘረኝነት ጥቃት ፈፅመዋል” ስትል ወቀሰች። ትራምፕ ኤልሃን ኦማርና ሌሎች ሶስት የምክር ቤት ሴት አባላትን ተችተው በትዊተር ገጻቸው መጻፋቸውን ተከትሎ የተለያዩ አስተያየቶች እየተስተናገዱ ነው። ከትዊተር ገጻቸው በተጨማሪ ለጋዜጠኞች በሰጡት ቃላቸውም “እነሱ ሀገራችንን ይጠላሉ፤ ደስተኛ ካልሆኑ ሀገራችንን ለቀው ይውጡ” ሲሉም ተደምጠዋል። ፕሬዚዳንቱ አራቱ የምክር ቤት አባላትን በወነጀሉበት ንግግራቸው “እንደ አልቃኢዳ ያሉ የአሜሪካ ጠላቶች ወዳጅ ናቸው” ብለዋል። ትችት የተሰነዘረባቸው ኤልሃን ኦማር፣ ኤለክሳንድሪያ ኦካሲዮ-ኮርቴዝ፣ አያን ፕሬስሌይ እና ራሺዳ ትላይብ የተሰኙት የምክር ቤት አባላትም በጉዳዩ ላይ መግልጫ ሰጥተዋል። ፕሬስሌይ “ትራምፕ መጤ ጠልና ጽንፈኛ ንግግር አድርገዋል፤ ዝም አንልም” ብላለች። ኤልሃን ኦማር በበኩሏ “ፕሬዚዳንቱ በአራቱ ሴት የምክር ቤት አባላት ላይ ቀለምን መሰረት ያደረገ የዘረኝነት ጥቃት ፈጽመዋል፤ ይህ ደግም የነጭ ብሔርተኛነት አጀንዳ ነው” ስትል ተሰምታለች። ሴት የምክር ቤት አባላቱ በመግለጫቸውም የአሜሪካ ህዝብ በትራምፕ ድርጊት ሆድ እንዳይብሰው መክረዋል። ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የዘረኝነት ጥቃት ፈፅመዋል በሚል ለቀረበባቸው ውንጀላ ሲመልሱ “አያሳስበኝም ብዙዎች በሀሳቤ ተስማምተዋል” ማለታቸውን የዘገበው ኤኤፍፒ ነው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም