ጋዜጠኛ መስፍን ሺፈራው ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ

104
ሀምሌ 9/2011 በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ለረጅም ዓመታት በጋዜጠኝነትና በሌሎች የስራ ዘርፎች ያገለገለው ጋዜጠኛ መስፍን ሺፈራው ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ። ጋዜጠኛ መስፍን ከአባቱ ከአቶ  ሺፈራው ኃይሉ እና ከእናቱ ከወይዘሮ ውቤ ገሰሰ በ1955 ዓ.ም በቀድሞ ሐረርጌ ክፍለ ሀገር ሀብሮ አውራጃ ቁኒ ወረዳ በዴሳ ቀበሌ ተወለደ። እድሜው ለትምህርት ሲደርስ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በበዴሳ አንደኛ፤ ደረጃ ሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በጨርጨር አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትሏል። የከፍተኛ ትምህርቱን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በጂኦግራፊ የትምህርት መስክ የመጀመሪያ ዲግሪውን አግኝቷል። በስራ ዓለምም በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት  ከተቀጠረበት  ከጥቅምት 10/1980 ዓ.ም ጀምሮ እስከ የካቲት 10/1998 ዓ.ም ድረስ በጋዜጤኝነት ሙያ በአዘጋጅነት፣ የሽፍት እንዲሁም የክልል ዜና ማስተባባሪያ ዴስክ ሀላፊ በመሆን አገልግሏል። እንዲሁም በኢዜአ የሲቪል ሰርቪስ ኃላፊና በድርጅቱ ከመቀጠሩ በፊት በማዕከላዊ ፕላን ጽህፈት ቤት ሰርቷል። መስፍን ሺፈራው ኢዜአን ከለቀቀ ከየካቲት 10 ቀን 1998 ዓ.ም በኋላም በዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከልና በሌሎች የመንግስት መስሪያ ቤት በተለያዩ  የስራ መስኮች ተመድቦ አገልግሏል። ጋዜጠኛ መስፍን ሺፈራው በባለሙያነትና በስራ ኃላፊነት ባገለገለባቸው ዓመታት ምስጉን እንደነበር ባልደረቦቹ ይመሰክራሉ። ከስራ ባልደረቦቹም ተግባቢ፣ ቅንና መልካም ግንኙነት ነበረው፤ በማህበራዊ ህይወቱም እንዲሁ። ጋዜጠኛ መስፍን ሺፈራው ባደረበት ህመም በህክምና ሲረዳ ቆይቶ በ56 ዓመቱ ሐምሌ 8 ቀን 2011 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል። ባለትዳርና የአንድ ወንድ እና የሁለት ሴት ልጆች አባት ነበር።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም