በመቐለ የ10 ኪሎ ሜትር ሩጫ ተካሄደ

96
መቐለ ኢዜአ ሐምሌ7/2011 በመቀሌ ከተማ በሁለቱም ፆታዎች የ10 ኪሎ ሜትር ውድደር ዛሬ ተካሄደ። ውድድሩ ስፖርት ባህል ያደረገ ጤናማ ማህበረሰብ ለመፍጠር ብሎም ክልሉንና አገር ወክለው የሚወዳደሩ አትሌቶች ለማፍራት ዓላማ ያደረገ እንደነበር ተገልጿል። መነሻውንና መድረሻው ሮማናት አደባባይ ባደረገው  ውድድር ከ9ሺህ የሚበልጡ አትሌቶችና የከተማው ማህበረሰብ ተሳትፏል። በሁለቱም ፆታ ከአንደኛ አስከ ሶስተኛ ደረጃ ይዘው  ውድድራቸውን ላጠናቀቁ አትሌቶች የገንዘብና የዋንጫ ሽልማት ተሰጥቷል። በወንዶች በተደረገው ውድድር አንደኛ የወጣው ገብረጅወርግስ ተክላይ 60ሺህ ብር ፤ሁለተኛ የወጣው ምሩፅ ውበት 30ሺህ ብር፤ሶስተኛ ለወጣው ኃይለማርያም ኪሮስ 20ሺህ ብር ተሸልመዋል። በተመሳሰይ በሴቶች ውድድሩን ያሸነፉት ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ በመውጣት ያሸነፉት ፈትየን ተስፋይ ፣ ጎይቶም ገብረስላሴና አበራሽ ምናሰቦ ሽልማቱን ተቀብለዋል። ለሶስተኛ ጊዜ በከተማው የተካሄደው ውድድር የተዘጋጀው አትሌት ገብረእግዚብሔር ገብረማርያምና ባለቤቱ ወርቅነሽ ኪዳነ ባቋቋሙት ናትና ስፖርት ኤቨንትስ በተባለ ተቋም ነበር። ውድድሩን ያስጀመሩት የትግራይ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ገነት አረፈ የማህበረሰቡ ስጋት እየሆኑ የመጡ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመፈወስ ዓይነተኛ መፍትሄ ስፖርት መሆኑ ማወቅና መተግበር አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም