ግብጽ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ስትራቴጂያዊ ግንኙነት ታጠናክራለች

63
ካይሮ ሰኔ 4/2010 ግብጽ የኢትዮጵያን ፍላጎት፣ ደህንነትና መረጋጋትን መሰረት ያደረገ ስትራቴጂያዊ ግንኙነቷን እንደምታጠናክር ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አል ሲሲ ገለጹ። የሁለት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድና  ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። የሁለቱ አገሮች መሪዎች በሁለትዮሽ ጉዳይ፣ በአህጉራዊና በዓለምአቀፋዊ ጉዳዮች ላይ በስፋት ተወያይተዋል። በተለይም አገሮቹ የጋራ ፍላጎታቸውን ሊያረጋግጥ የሚችል አካባቢያዊ ትስስር ለመፍጠር በሚያስችሉ ነጥቦች ላይ መግባባት ላይ ደርሰዋል። ውይይቱ ቀደም ሲል የነበረውን የጥርጣሬ መንፈስ ሊያከስም በሚችል መልኩ መወያየታቸው ነው የተገለጸው። ፕሬዚዳንት አል ሲሲ በፕሬስ  መግለጫው ላይ እንደተናገሩት፤ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ስትራቴጂያዊ አጋርነት ነው። የግብጽ ስትራቴጂ ደግሞ የሁለቱን የጋራ ፍላጎት ማረጋገጥ ነው። ግብጽ የምታራምደው ፖሊሲ የኢትዮጵያን ፍላጎት፣ መረጋጋትና ደህንነትን መሰረት ያደረገ መሆኑን ነው ፕሬዚዳንቱ ያረጋገጡት። ሁለቱ አገሮች የኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ የማንንም ጥቅም በማይነካ መልኩ እንዲከናወን ስምምነት ላይ ለመድረስ ላለፉት አራት ዓመታት በጋራ ሲሰሩ እንደነበር ያስታወሱት ፕሬዚዳንት አል ሲሲ፤ ለኢትዮጵያ ህዝቦች የመልማት ፍላጎት ተግባራዊነት  አጽንኦት እንደሚሰጡ አረጋግጠዋል፡፡ ፕሬዚዳንት አል ሲሲ እንደገለጹት፤ በውይይቱ ወቅት በኢትዮጵያ ያሉትን የግብጻውያን ኢንቨስተሮች ቁጥር ለማሳደግ ስምምነት ላይ ደርሰዋል። በኢትዮጵያ ውስጥ የግብጽ ኢንዱስትሪ ፓርክ በመመስረት ለኢንቨስተሮቹ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጠርም ቃል እንደተገባላቸው አውስተዋል። በግብጽ፣ በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል የመሰረተ ልማት ዝርጋታን ለማፋጠን የፋይናንስ ፈንድ ማቋቋም ጉዳይ ትኩረት እንደሚሰጠውም ተናግረዋል። በኢትዮጵያ የፌዴራል የስራ ቋንቋ የፕሬስ መግለጫውን የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ፤ ኢትዮጵያ ወንድም የሆነውን የግብጽ ህዝብ በፍጹም የሚጎዳ ነገር እንደማታደርግ አረጋግጠዋል። “እኛ ኢትዮጵያዊያን ወንድምነትና ጉርብትና የምናውቅ፤ እግዚአብሔርን የምንፈራ ስለሆንን ወንድም ህዝብ የሆነውን የግብጽ ህዝብ በፍጹም፣ በፍጹም የመጉዳት ሃሳብም ፍላጎትም የለንም” ብለዋል። ኢትዮጵያ የአባይን ወንዝ ማልማት እንደምትችልና እንደሚገባት የምታምን መሆኑን ያመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ነገር ግን የራሷን ልማት ስታካሂድ “ግብጽን ወይም ሱዳንን መጉዳት አለብን የሚል እምነት በፍጹም የለንም” ሲሉ አረጋግጠዋል። በኢትዮጵያና በግብጽ መላካከል የሚኖረው ግንኙነት አንዱ አንዱን የሚያግዝ፣ የሚተባበር፣ ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ፣ አንዱ አንዱን ማገዝ የሚችልበት አቅጣጫ የመከተል አስፈላጊነት ላይ ከፕሬዚዳንቱ ጋር መግባባታቸውን ጠቁመዋል። በአፍሪካ ውስጥ ላለፉት መቶ ዓመታት አንዱ አንዱን ለመጣል ሲያሴር ቢቆይም ማንም ግን አሸናፊ ሆኖ ያለመውጣቱን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤  የማሸነፊያው መንገድ ትብብርና በጋራ መስራት መሆኑን ገልጸዋል። በሰላምና በፍቅር በልማት በመስራት አካባቢውን ለመቀየር ስምምነት መድረሳቸውን ነው ያመለከቱት። የመገናኛ ብዙሃን ላለፉት መቶ ዓመታት የጥላቻ ፖለቲካ አጀንዳ እየቀረጹ ሲሰሩ መቆየታቸውን አስታውሰው፤  ህዝብን ከህዝብ በሚያገናኝ፣ በሚያቀራርብ፣ ልማትን በሚያፋጥን ተግባር ላይ  ብቻ አተኩረው እንዲሰሩ አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም