የሃይማኖት አባቶች እርስ በእርስ መግባባትና የአንዱ ለሌላው ሃይማኖት ጥብቅና መቆም ለዓለም ሰለም መሰረታዊ መሆኑ ተገለጸ

97
ሐምሌ 6/2011 (ኢዜአ) ሃይማኖቶች ለሰላም መስፈን የሚያደርጉትን አስታዎጾኦ ለመጠቀም የሃይማኖት አባቶች እርስ በእርስ መግባባትና የአንዱ ለሌላው ሃይማኖት ጥብቅና መቆም እንደሚገባ እውቁ የዓለም አቀፍ የሃይማኖት ነፃነት ተቋም አምባሳደር ሳም ብራውንባክ ገለጹ። አምባሳደሩ የሃይማኖት ነፃነትን በዓለም ዙሪያ እንዴት ማስፋፋት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ከመላው አለም ከተውጣጡ ጋዜጠኞች ጋር በስልክ ውይይት አድርገዋል። አምባሳደር ሳም ብራውንባክ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት በምድራችን አስተማማኝ ሰላም ለማረጋገጥ ዓለም አቀፉ ህብረተሰብ የሃይማኖት ነፃነትን ማረጋገጥ ይኖርበታል። ይህም በአለም አቀፍ ደረጃ ሰላም እንዲሰፍን ከመርዳቱም በላይ ሰዎች  እርስ በእርስ እንዲተሳሰቡ፣ እንዲዋደዱና እንዲከባበሩ ያደርጋል ብለዋል። ለዚህም የሃይማኖት አባቶች እርስ በእርስ መግባባትና የአንዱ ኃይማኖት አባት ለሌላው ሃይማኖት ጥብቅና መቆም እንደሚገባቸው ተናግረው፣ ሃይማኖት የሰላም መሰረት መሆኑን መናገርና መስበክም ያስፈልጋል ሲሉ ገልጸዋል። ሃይማኖቶች የተለያዩ ዓይነት አስተምህሮ ቢኖራቸውም ለሰላም ቅድሚያ እንደሚሰጡ የታወቀ መሆኑን ጠቅሰውም የሃይማኖት ነፃነትን ማክበር እርስ በእርስ መረዳዳትና የሰብዓዊ መብት እንዲጠበቅ በማድረግ ለሰላም የራሱን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም