የቃሊቲ የየብስ ትራንስፖርት ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቱ በካይዘን ትግበራ 27 ሚሊዮን ብር አተረፈ

101
ሀምሌ 6/ 2011(ኢዜአ) የቃሊቲ የየብስ ትራንስፖርት ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ካይዘን ትግበራ 27 ሚሊዮን ብር በላይ ማትረፍ መቻሉን ገለፀ። የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት የቃሊቲ የየብስ ትራንስፖርት ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት የመጀመሪያ ዙር የካይዘን ትግበራ ውጤቱ ተገምግሟል። ድርጅቱ በአንድ አመት ውስጥ ባስመዘገበው የካይዘን የመጀመሪያ ዙር ትግበራ አመርቂ ውጤት ያስመዘገበ ሲሆን በተያዘው በጀት አመት ወደ ሁለተኛው ዙር ትግበራ ተሸጋግሯል። የፅህፈት ቤቱ ዳይሬክተር አቶ ተሰማ ፎቴ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ከአንድ አመት በፊት በፅህፈት ቤቱ ምቹ የስራ ከባቢ አልነበረም፤ ንብረቶቹም ለብክነት ተዳርገው ነበር። ካይዘን መተግበር ከጀመረ ወዲህ ግን በሰራተኛው ላይ ከፍተኛ የስራ ተነሳሽነት ስሜት መፈጠሩን ገልፀዋል። በዚህም አገልግሎታቸውን የጨረሱ ጎማና ባትሪን የመሳሰሉ መለዋወጫዎችን በጨረታ በመሸጥ ከ11ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን ገልፀው፤ በፅህፈት ቤቱ በሚገኘው የማሽን ሾፕ ከውጭ ይገዙ የነበሩ ምርቶችን ማምረት መቻሉንም ተናግረዋል። በእነዚህም ተግባራት ከ27 ሚሊዮን ብር በላይ ማትረፍ መቻሉንም ነው ዳይሬክተሩ ያስረዱት። ለረጅም ጊዜ ያለ አገልግሎት የቆዩ እንደውሃ ማጣሪያ የመሳሰሉ መሳሪያዎችን አገልግሎት እንዲሰጡ በማድረግም ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ እንዳዳነም በመግለፅ። አገልግሎትን በማቀላጠፍ አንድ ሰራተኛ መሳሪያዎችን ለመፈለግ ይፈጅበት የነበረውን 30 ደቂቃ ወደ ሁለት ደቂቃ መቀነስ አስችሏልም ብለዋል። ፅህፈት ቤቱ ይህን ያገኘውን ልምድ ለሌሎች መስሪያ ቤቶች ማካፈሉን የገለፁት አቶ ተሰማ፤ በቀጣይም ካይዘንን ሙሉ በሙሉ በመተግበር ወደ ፈጠራ ስራ እንደሚገባም ነው የጠቆሙት። የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሮባ መገርሳ በበኩላቸው ፅህፈት ቤቱ በድርጅቱ ለብክነት የተጋለጠ አሰራር የነበረው መሆኑና ከፍተኛው የድርጅቱ ንብረቶችም በፅህፈት ቤቱ ውስጥ መገኘታቸው ለትግበራ የመጀመሪያ ተመራጭ አድርጎታል። አሁን ላይ በፅህፈት ቤቱ የታየው ለውጥ የሀብት ብክነትን መቆጣጠር ያስቻለና ለሰራተኞችና ደንበኞች ምቹ ሁኔታን የፈጠረ በመሆኑ ወደ ሌሎች ቅርንጫፎችም ለማስፋት መታቀዱን ነው የተናገሩት። የኢትዮጵያ ካይዘን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮንን ያኢ ፅህፈት ቤቱ ያስመዘገበው ውጤት የድርጅቱ አመራርና ሰራተኞች ለትግበራው የነበራቸው ፍላጎት ማሳያ ነው ብለዋል። ፅህፈት ቤቱ ለሌሎች ድርጅቶች የተሞክሮ መቀመሪያ ተደርጎ የሚወሰድ መሆኑን ገልፀው በቀጣይም ለዚህ ተግባርና ለቀጣይ የካይዘን ዙር ትግበራ የሚያከናውነውን ተግባር እንደግፋለን ነው ያሉት። ካይዘን የጃፓን የምርታማነትና የጥራት ፍልስፍና ሲሆን የአሰራር ልምዶችንና ብቃትን በቀጣይነት ለማሻሻል የሚያስችል የአሰራር ፍልስፍና ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም