የአሰራር ፍትሀዊነትና ግልፅነት መጓደል በስራችን ላይ ጫና እያሳደረብን ነው –  በጥቃቅና አነስተኛ  የተደራጁ ማህበራት

991

ሰኔ 4/2010 በአሰራር ሂደት የሚስተዋሉ የግልጽነትና የፍትሃዊነት ችግሮች በስራቸው ላይ ጫና እያሳደሩባቸው መሆኑን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጥቃቅና አነስተኛ ተደራጅተው በግንባታው ዘርፍ የተሰማሩ አስተያየት ሰጪዎች ተናገሩ፡፡

አብዮት አወቀ ከጓደኛው ጋር በአነስተኛና ጥቃቅን ተደራጅቶ ዘርፉን ከተቀላቀለ አራት ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡

ማህበራቸው በአብዛኛው ህንጻዎችን የማጠናቀቅ ስራዎችን እንደሚሰራ ያብራራው አብዮት እንደ ስራው ስፋትና ጥበት ከ40 እስከ 50 ለሚሆኑ ሰራተኞች የስራ እድል ይፈጥራል፡፡

ይሁን እንጂ ፍትሃዊና ግልጽነት የተሞላበት የአሰራር ስርዓት አለመኖሩ በስራው ላይ ተጽዕኖ እያሳደረበት መሆኑን ነው ወጣቱ የተናገረው፡፡

ለዚህም የተወሰኑ ማህበራት ተደጋጋሚ ስራ እንደሚሰጣቸውና የእርሱን ጨምሮ ሌሎች ማህበራት ደግሞ እድሉን በሚፈለገው ልክ እያገኙ አለመሆናቸውን በማሳያነት  ጠቅሷል፡፡

ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ በዝርፉ የተሰማራው ግርማ አበራም እስከ 70 ለሚደርሱ ወጣቶች የስራ እድል እየፈጠረ ቢሆንም ግልጽነት በጎደለው መልኩ ስራዎቸ በሌላ ክፍለ ከተማ ለተደራጁ ማህበራት የሚሰጥበት አሰራር ቅሬታ እንዳሳደረበት ተናግሯል፡፡

የአሰራር ፍትሃዊነትና ግልጽነት ችግሮች ቢቀረፉ ድርጅቱ ካፒታሉን ይበልጥ የሚያሳድግበትና ለወጣቶችም ተጨማሪ የስራ እድል የሚፈጥርበት እድል እንደሚሰፋም ነው የገለጸው፡፡

ዘርፉን  ከተቀላቀለ  ሶስት  አመታትን  ያስቆጠረው ጌታሁን  ምትኩ  ደግሞ  ለጥቃቅንና አነስተኛ  የሚሰጠውን የተዛባ  ትርጓሜ  ጨምሮ የጫራታዎች  ግልጽነት  መጓደልና የሚቀርበው ዋጋ ወቅቱን ያገናዘበ አለመሆን በዘርፉ ለመዝለቅ ጫና እንዳሳደረበት ተናግሯል፡፡

በጥቃቅንና  አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ የኮምዩኒኬሽን  ዳይሬክተሩ አቶ  ሞላልኝ ባዩ እንዳሉት ለስራ በተፈለጉበት ጊዜ ሳይሆን ራሳቸው በሚፈልጉበት ጊዜ የሚመጡ ማህበራት አሉ፤ አንዳንድ ዘርፎች ደግሞ በባህርያቸው የስራ ጥበት ያለባቸው በመሆናቸው ችግሮቹ ሊከሰቱ እንደሚችሉ ነው የገለጹት፡፡

ያም ቢሆን ካለፉት ሁለት ወራት ወዲህ  ቢሮው  በሚፈለገው ልክ  የእድሉ ተጠቃሚ  ያልሆኑ ኢንተርፕራዞችን  እየለየ ስራ እየሰጣቸው  መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በስራ ክፍፍል ጊዜ የኢንተርፕራይዙ አባላት ቁጥርና የስራ ልምዳቸው ከግምት ውስጥ እንደሚገባ ያብራሩት ዳይሬክተሩ የተወሰኑ ድርጅቶች ከተቋማት ጋር ባላቸው የስራ ግንኙነት ስራቸውን ካላስቀጠሏቸው በስተቀር ሆን ተብሎ አድልኦ እንደማይፈጸም አብራርተዋል፡፡

አቶ ሞላልኝ እንዳሉት ጫራታ ሲካሄድ በጥቃቅንና አነስተኛ ለተደራጁ ማህበራት ዋስትና ይሰጣቸዋል፤ የቅድሚያ ክፍያና የውል ማስከበሪያ ክፍያ አይጠየቁም፤ ሶስት በመቶ ማበረታቻም ይደረግላቸዋል፡፡

ከዚህ ባለፈ ቢሮው ጫራታውን በሚያወጣው ተቋም ላይ ጣልቃ መግባት እንደማይችልም ነው የተናገሩት፡፡

ቢሮው በዘርፉ መሰማራት የሚፈልጉትን  የማደራጀት፣ የስራ እድል አማራጮችን  የመለየትና የማስፋት እንዲሁም የገበያ ትስስር የመፍጠር ስራዎችን ይሰራል፡፡