በኢሉአባቦር ከ130 በላይ ሔክታር አሲዳማ መሬት ታከመ

2396

መቱ ሰኔ 3/2010 በኢሉአባቦር ዞን በተያዘው ዓመት ከ130 ሄክታር በላይ አሲዳማ አፈር በኖራ መታከሙን  የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

በጽህፈት ቤቱ  የአፈር  ለምነትና ስርጸት ቡድን መሪ አቶ ሂርጶ ሞርካ  ለኢዜአ እንደገለጹት በዞኑ ከዚህ ቀደም ወደ አሲዳማነት የሚቀየር አፈር እምብዛም አልነበረም፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አርሶአደሮች በማሳቸው አንድ አይነት ሰብል ደጋግመው በማልማታቸው የአፈር አሲዳማነት እየተፈጠረ መጥቷል፡፡

በማሳ ላይ የዝናብ መብዛትም አፈር ውስጥ ያለውን ንጥረ ነገር በማጠብ አፈሩ ወደ አሲዳማነት እንዲቀየር አስተዋጽኦ እንዳለው ያመለከቱት   ቡድን መሪው በተያዘው ዓመት በኖራ የታከመው መሬት በመቱ፣ያዮ፣ ቡሬ፣ ሁሩሙ  እና አሌ ወረዳዎች  ከ450 የሚበልጡ አርሶአደሮች ንብረት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አሲዳማ አፈሩን ለማከም ከ2ሺ ኩንታል በላይ ኖራ ከጉደር ኖራ ፋብሪካ በማስመጣት ጥቅም ላይ እንደዋለ ነው የገለጹት፡፡

በኖራ ከታከመው በተጨማሪ በስምንት ወረዳዎች በ175 ሄክታር በላይ  የአሲዳማነት ምልክት በመታየቱ ናሙና ተወስዶ እየተመረመረ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

አርሶአደሩ የአፈር አሲዳማነትን ለመከላከል ሰብል አፈራርቆ እንዲዘራ ተከታታይ ትምህርት እየተሰጠ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የአፈር ለምነትን ለመጠበቅም የተፈጥሮ ማዳበሪያና በማብላላት የሚያዘጋጁ የትል ዝርያዎችን ለአርሶአደሩ በማስተዋወቅ ሁሉም አርሶአደሮች የተፈጥሮ ማዳበሪያ እንዲጠቀሙ ለማድረግ እየተሰራ ነው፡፡

በዞኑ መቱ ወረዳ ቡሩሳ ቀበሌ አርሶአደር አለማየሁ ጉግሳ በሰጡት አስተያየት የእርሻ ማሳቸው አፈር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መልኩ ወደ ቀይነት በመቀየር ሰብል እያቀጨጨባቸው መቸገራቸውን  ተናግረዋል፡፡

አርሶ አደሩ እንዳሉት የተፈጥሮ ማዳበሪያን በመጠቀምና በኖራ በማከም  ምርታማነቱን ለማሳደግ ጥረት እያደረጉ ናቸው፡፡

በየጊዜው ለሚፈጠረው የአፈር ለምነት መቀነስ ቀድሞ ለመከላከል በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና የተፈጥሮ ማዳበሪያ አዘገጃጀት ላይ እየሰሩ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ ሌላኛው የቀበሌው አርሶአደር ጉደታ ነገዎ ናቸው፡፡

በኢሉአባቦር በ2010/2011 የምርት ዘመን  ከ145ሺ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብል ለማልማት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡