ለጤና አስጊ ሆነው የተገኙ 110 የምግብና መድሃኒት ዓይነቶች እንዲወገዱ ተደረገ

95
አዳማ  ሐምሌ 06/2011 /ኢዜአ/ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በተደረገው ክትትልና ቁጥጥር ለህብረተሰቡ ጤና አስጊ ሆነው የተገኙ 110 ዓይነት የምግብ ምርቶች ከገበያ ላይ መወገዳቸውን የኢትዮጵያ የምግብ መድኋኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደር ቁጥጥር ባለስልጣን ገለፀ። ባለስልጣኑ በ2011ዓ.ም  የበጀት ዓመት አፈፃፀምና በተያዘው የስራ ዘመን እቅድ ዙሪያ  በአዳማ ከተማ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየመከረ ይገኛል። በምክክር መድረኩ የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሪት ሄራን ገርባ እንደገለጹት ለህብረተሰቡ ጤና ጠንቅ ሆነው የተገኙ መድኃኒቶች፣ የህክምና መሳሪያዎች፣ የተለያዩ የምግብ ዓይነቶችና ሸቀጦች አገልግሎት ላይ እንዳይውሉ መደረጉን ገልጸዋል። ሀገር ውስጥ ከተመረቱ የምግብ ዓይነቶች መካከል በተለይም የጥራት ችግር የተገኘባቸው  በርበሬ፣ እንጀራ፣ ማር፣ ቅቤና ዘይትን ጨምሮ ችግር አለባቸው የተባሉ ሌሎች ምርቶች እንዲወገዱ ተደርጓል ። ከውጭ ሀገር ከገቡ ምርቶች ደግሞ  ከ5 ሺህ ቶን በላይ መድኃኒቶች፣ የህክምና መሳሪያዎች፣ የተለያዩ የምግብ ዓይነቶችና ሸቀጦች ጥራታቸውን ያልጠበቁ፣ የመጠቀሚያ አገልግሎት ጊዜያቸው ያበቃ፣  የተመረቱበት ሀገርና ኩባንያዎች በውል የማይታወቁ ሆነው በመገኘታቸው ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ተደርጓል። ዳይሬክተሯ እንዳሉት በ17 የመግቢያና መውጫ የመቆጣጠሪያ ኬላዎች፣ በአዲስ አበባና ሁሉም ክልሎች የተቀናጀ ርብርብ በመደረጉ በበጀት ዓመቱ   የተሻለ አፈፃፀም ተመዝግቧል። በአዲስ አበባና ፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ጠንካራ ክትትልና ቁጥጥር በመደረጉ በምግብ ምርቶች ላይ እየተፈፀመ ያለው ወንጀል መቀነሱን ጠቅሰው "በአሁኑ ወቅት ወደ ክልሎች በመሸሽ ተመሳሳይ ወንጀል እየፈፀሙ መሆኑን ደርሰንበታል "ብለዋል። "በተያዘው የበጀት ዓመት አዲስ አበባን ጨምሮ በሁሉም ቦታዎች ጠንካራ ክትትልና ቁጥጥር የማድረግ ተግባር በተቀናጀ መልኩ ጀምረናል " ያሉት ዳይሬክተሯ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ላይ የሚደረገው ቁጥጥር ደግሞ  ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል። የኦሮሚያ ጤና ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ በበኩላቸው በክልሉ ባሉት የመግቢያና መውጫ ኬላዎች በተለይም በኬንያና ሱዳን ድንበር በኩል ከውጭ በሚገቡ የምግብ ምርቶች፣ የህክምና መሳሪያዎችና መድኃኒቶች ቁጥጥር ላይ በጋራ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል። ጥራታቸው የወረደ የህክምና መገልገያ መሳሪያዎችና መድኃኒቶች ጥቅም ላይ ሲያውሉ የተገኙ ብዛት ያላቸው  ተቋማት እንዲዘጉ መደረጉን ጠቅሰው መድኃኒቶችን ጨምሮ ሌሎች ለጤና አስጊ የሆኑ ምርቶች መወገዳቸውን ገልጸዋል። "አሁንም ከባለስልጣኑ ጋር በትብብር በመስራት ለህብረተሰቡ ጤና ጠንቅ የሆኑ ምርቶች ከገበያ ላይ እንዲወገዱ እርምጃ የመወሰድ ተግባሩን ተጠናክሮ ይቀጥላል" ብለዋል። በአዳማ ለሁለት ቀናት በሚቆየው የምክክር መድረኩ ከክልሎችና ከፌዴራል መስሪያ ቤቶች የተወጣጡ ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።                
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም