በማህበረሰብ አቀፍ የህጻናት ድጋፍ መርኃ ግብር ከ5 ሚሊዮን በላይ ህጻናት እንክብካቤ እየተደረገላቸው ነው

3870

አዲስ አበባ ሰኔ 3/2010 በማህበረሰብ አቀፍ የህጻናት ድጋፍ መርኃ ግብር ከ5 ሚሊዮን በላይ ህጻናት እንክብካቤ እየተደረገላቸው መሆኑን የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

የአፍሪካ ህጻናት ቀንን ምክንያት በማድረግ የሚኒስቴሩ ከፍተኛ አመራሮች፣ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህጻናትና ሴቶች ጉዳይ ቋሚ ከሚቴ አባላት ስለ እናት ህጻናት ማሳደጊያ በጎ አድራጎት ድርጅትን ጎብኝተዋል።

ሚኒስትር ደኤታዋ ወይዘሮ አለሚቱ ኡሞድ እንደተናገሩት፣ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ህጻናት በማህበረሰቡ ባህል ወግና እሴት ታንጸው እንዲያድጉ አማራጭ የህጻናት ድጋፍና እንክብካቤ አገራዊ መርሀ ግብሮች እየተተገበሩ ነው።

በእነዚህ መርሃ ግብሮች ከ 5 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ህጻናት ማህበረሰብን መሰረት ያደረገ ድጋፍ በማግኘት ላይ መሆናቸውን ወይዘሮ አለሚቱ ተናግረዋል።

እንዲያም ሆኖ በበርካታ ውስብስብ ችግሮች ውስጥ ያሉ ህጻናት፣ ወላጅ የሌላቸው ህጻናት ቁጥር ቀላል እንዳልሆነ የገለጹት ሚኒስትር ደኤታዋ ሁሉም ዜጋ የበኩልን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

በተለይም ሴቶችና ህጻናት ወደ ጎዳና እንዳይወጡ፣ራሳቸውን የሚችሉበትን ሁኔታ የማቻቸት የጎዳና ህይወት የሚመሩትን ወደ ማህበረሰቡ የመቀላቀል እንቅስቃሴው ዘላቂ እንዲሆን ሁሉም አካላት በባለቤትነት ስሜት ሊረባረቡ ይገባል ብለዋል።

የቋሚ ኮሚቴው ተወካይ አቶ ሰጠኝ አዲሱ በበኩላቸው የነገ አገር ተረካቢ ትውልድ የዛሬ ህጻናት መሆናቸውን ከግምት በማስገባት ህጻናት የመልካም ስብዕና ባለቤት እንዲሆኑ በትኩረት መስራት እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ስለ እናት በጎ አድራጎት ድርጅት እየሰራ ያለው ሥራ ለሌሎችም አርአያ የሚሆን መሆኑን ገልጸው ኅብረተሰቡም ትልቅ ኃላፊነት እንዳለበት አመልክተዋል።

ምክር ቤቱ በህጻናት ጉዳይ ዙሪያ የሚከናወኑ ተግባራትን ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የስለ እናት የህጻናት ማሳደጊያ በጎ አድራጎት ማህበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ያሬድ አብዱ እንደተናገሩት፣ ማህበሩ ለችግር ለተጋለጡ ህጻናት የመጠለያ፣ የምግብ፣ የልብስ፣ የጤና እና መሰል እንክብካቤና ድጋፎችን እየሰጠ ነው።

በተለይ ከኤች አይ ቪ ኤድስ ቫይረስ ጋር አብረው ለሚኖሩ ወገኖች እስካሁን በድሬዳዋ፣ በሀዋሳ፣ በኢሊባቡር፣ በአሶሳ፣ በጂንካ፣ በሻሸሜኔና በአዲስ አበባ ከ 4 ሺህ በላይ ህጻናትንና ከ 450 በላይ እናቶችን መደገፉን ተናግረዋል።

በአስከፊ ድህነት ውስጥ ለነበሩና ትምህርታቸውን ለማቋረጥ ተቃርበው ለነበሩ 200 ተማሪዎች ድጋፍ በመስጠት ከትምህርት ገበታቸው እንዳይርቁ መደረጉን አብራርተዋል።

እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለጻ በማህበሩ እስካሁን ለ1 ሺህ ተማሪዎች የትምህርት እድል የተሰጠ ሲሆን ከነዚሁ ውስጥ 19ኙ ተመርቀው ቤተሰቦቻቸውን እየረዱ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የአፍሪካ ህጻናት ቀን በአፍሪካ ለ28ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ27ኛ ጊዜ ሰኔ ዘጠኝ ይከበራል።