ተመራቂ ተማሪዎች ለህፃናት ማሳደጊያ የምግብና የአልባሳት ድጋፍ አደረጉ

116
ሀምሌ ሀረር (ኢዜአ) 5/2011 የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የዘንድሮ የቴክኖሎጂ ተመራቂ ተማሪዎች በሐረር ከተማ ለሚገኝ አንድ የህጻናት ማሳደጊያ ማዕከል የአልባሳትና የምግብ ድጋፍ አደረጉ። በ2008 ዓ.ም በሀረር ከተማ ሸንኮር ወረዳ ቀበሌ አስር  ውስጥ  የተመሰረተው ”ሐረር የአገር ልጅ የበጎ አድራጎት ማዕከል” 75 ህጻናትን በውስጡ አቅፎ በመያዝ ይንከባከባል ። ከማዕከሉ ውጭ ደግሞ 500 ለሚሆኑ ህፃናት የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል። በሀረማያ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ተመራቂ ተማሪዎች የልብስና የምግብ ቁሳቁሶችን በማሰባሰብ በማዕከሉ ለሚገኙ ወላጆቻቸውን ላጡ  ህፃናት አስረክበዋል ። በዩኒቨርሲቲው የቴክኖሎጂ ተማሪዎች ተወካይ ተማሪ ዳዊት ደሱ በሰጠው አስተያየት "የዘንድሮው ተመራቂ ተማሪዎች በበጎ ፈቃድ ተነሳስተን ወላጆቻቸውን ያጡ ህፃናትን ለመደገፍ የጀመርነውን ጥረት በምንሔድበት ቦታ ሁሉ አጠናክረን እንቀጥልበታለን" ብሏል ። የተቸገሩ ህፃናትን መርዳት የህሊና እረፍትና ደስታ እንደሚሰጥ የተናገረው ደግሞ ተማሪ ረዛቅ ናስር ናው፡፡ ከቴክኖሎጂው ተማሪዎች ያሰባሰቡትን  ግምቱ ከ10ሺ ብር በላይ የሆነ የምግብና አልባሳት ድጋፍ የመጀመሪያ እንጂ የመጨረሻቸው እንደማይሆን ገልጿል። ሁሉም ተማሪ ካለው  ላይ በመቀነስና በመቆጠብ በእንደዚህ ዓይነት በጎ ተግባር መሳተፍ እንዳለበትም መልዕክቱን አስተላልፏል። ”ሐረር ያገር ልጅ በጎ አድራጎት ማህበር ”መስራችና ስራ አስኪያጅ ወጣት ተስፋ አለባቸው  ተመራቂ ተማሪዎቹ  ለወገናቸውና ለሀገራቸው ያላቸውን ፍቅር የገለፁበት መንገድ በማድነቅ ሌሎችም አቅማቸውን በቻለው መጠን ወላጆቻቸውን ያጡ  ህፃናትና አቅመ ደካሞችን እንዲረዱ ጥሪ አቅርበዋል ። የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ዘንድሮ በተለያዩ የትምህርት ዘርፍ ካስመረቃቸው 7 ሺህ 273 ተማሪዎች መካከል 689 የቴክኖሎጂ ተማሪዎች ናቸው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም