የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በአሜሪካ የንግድ ምክር ቤት ስር ከሚገኙ ኩባንያዎች የስራ ሃላፊዎች ጋር መከሩ

68
ሐምሌ  4/2011 (ኢዜአ) የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ከአሜሪካ የንግድ ምክር ቤት ስር ከሚገኙ ኩባንያዎች የስራ ሃላፊዎች ጋር ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል። ከፕሬዚዳንቱ ጋር የተወያዩት ከ20 በላይ የሚሆኑ ኩባንያዎች ሲሆኑ ኢነርጂ፣ ትምህርት፣ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ ጤና፣ ፋይናንስና ቱሪዝም ደግሞ ኩባንያዎቹ ከተሰማሩባቸው የስራ መስኮች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። የኩባንያዎቹ ልዑክ መሪ የአሜሪካ የንግድ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንትና የኩባንያው የዓለም አቀፍ ጉዳዮች ሃላፊ ሚስተር ማይረን ብሪሊያንት ውይይቱ የአሜሪካ የቢዝነስ ማህበረሰብ በኢትዮጵያ ያለውን ተሳትፎ ይበልጥ ለማሳደግ በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ መሆኑን ተናግረዋል። በተለይም ኩባንያዎቹ በጤና ክብካቤ፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ በትምህርና በሌሎች መስኮች መስራት በሚችሉበት ሁኔታ እንዲሁም የኢትዮጵያ መንግስት በአሁኑ ሰዓት የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ እንደሚሻና በዚህም ኩባንያዎቹ በሚኖራቸው ተሳትፎ ላይ መምከራቸውንም ገልጸዋል። ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴም ኩባንያዎቹ በተለያዩ መስኮች መዋዕለ ነዋያቸውን አፍስሰው የኢትዮጵያና የአሜሪካን ግንኙነት በማጠናከር ላይ እንዲሰሩ መግለጻቸውንም አመልክተዋል። አሁን ያለው መንግስት ዘርፈ ብዙ በሚባሉ ጉዳዮች ለውጥ እያደረገ እንደሆነና ተጨማሪ የማሻሻያ ስራዎችን ለማከናወንም ፍላጎት እንዳለው ያወሱት ሚስ ማይረን፤ ይሄንን ለውጥ አሜሪካ በትኩረት የምትደግፈው መሆኑንም ነው ያስረዱት። የአሜሪካ የንግድ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ከአሜሪካ አልፎ በዓለም ላይ ከሚገኙ የቢዝነስ ተቋማት ጋር እነደሚሰራም ጠቅሰው የዛሬው ውይይትም  ኩባንያዎቹ በምን ዘርፎች መሰማራት እንደሚችሉና የሚደረግላቸውን ድጋፍ አስመልክቶም መረጃ ያገኙበት ነውም ብለዋል። በውይይቱ ወቅት ከፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ያገኙት ምላሽና መልክቶችም አበረታች እንደሆነና የአሜሪካ የግሉ ዘርፍ በኢትዮጵያ የአጭር ጊዜ ሳይሆን የረጅም ጊዜና ዘላቂነት ያለው የኢንቨስትመንት ስራ ለማከናወን ቁርጠኛ መሆኑንም አረጋግጠዋል። ምክር ቤቱ ከኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ጋር በትብብር እየሰራ እንደሚገኝም አመልክተዋል። የዛሬው ውይይትም ምክር ቤቱ ለሚሰራው ስራ እንደ መነሻ እንደሚያገለግልም እንዲሁ። የአሜሪካ የንግድ ምክር ቤት እ.አ.አ በ1912 የተተቋቋመ ዓለም አቀፍ የቢዝነስ ተቋም ሲሆን ከ3 ሚሊዮን በላይ ኩባንያዎችና የቢዝነስ ተቋማትን የሚወክል ነው። ኢትዮጵያና አሜሪካ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እ.አ.አ በ1903 ነው። ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከሚገኙ የአሜሪካ የልማት አጋሮች በዋነኛነት የምትጠቀስ ሲትሆን አገሪቷ በአሜሪካ የልማት ተራድኦ ድርጅት(ዬ ኤስ አይዲ) በኩል በጤና፣ በትምህርት፣ በግብርና፣ በምግብ ዋስትናና በሌሎች የልማት መስኮችም ድጋፍ የሚታገኝ አገር ናት። አሜሪካ ለአፍሪካ ሀገራት የሰጠችው ከቀረጥና ታሪፍ ነፃ የገበያ ዕድል (አጎዋ)  አማካኝነት የተለያዩ ምርቶቿን ወደ አሜሪካ በመላክ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ በመሆን ላይም ትገኛለች። በተጨማሪም ኢትዮጵያ ሽብርተኝነትን በመዋጋትና በደህንነት ጉዳዮች ላይ ከአሜሪካ ጋር በቅርበት ትሰራለች።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም