ወደ ወለጋ ስታዲዮም የሚወስደው የአስፋልት መንገድ ግንባታ ተጠናቀቀ

70
ነቀምቴ ሰኔ  3/2010 በነቀምቴ ከተማ ከ28 ሚሊዮን ብር በላይ በሚበልጥ ወጪ ወደ ወለጋ ስታዲዮም የሚወስደው የውስጥ ለውስጥ  የአስፋልት መንገድ ግንባታ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ። በኢትዮያጵያ  መንገዶች ባለስልጣን የፕሮጀክቱ ግንባታ ቡድን መሪ ኢንጂነር  ቃለአብ ጌታሁን እንደገለጹት  ወደ ስቴዲዮሙ የሚወስደው  የአስፋልት መንገድ  ግንባታ በሶስት አቅጣጫ የተሰራ  841 ሜትር  ርዝመትና  እስከ 15 ሜትር ስፋት ያለው ነው ። የአስፋልት መንገዱ  ግንባታ የከተማው አስተዳደርና የአካባቢው ህብረተሰብ ላቀረቡት ጥያቄ የተሰጠ መልስ መሆኑን አመልክተው  ባለስልጣኑ ከ28 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ማድረጉንም ተናግረዋል ። "ግንባታው በ2009 ዓ.ም ተጀምሮ በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ የተጠናቀቀ ነው" ብለዋል ። መንገዱ ተጠናቆ ለአገልገሎት ከፍት የሆነው ባለፈው ወር ውስጥ እንደሆነ ተመልክቷል፡፡ የወለጋ ስታዲዮም  ግንባታ አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ተሾመ ገመዳ በሰጡት አስተያየት  ወደ ስታዲዮሙ  የሚወስደው የአስፋልት መንገድ ግንባታ አካባቢውን ከማሳመሩም በላይ የህብረተሰቡን የመንገድ ችግር ጥያቄ የመለሰ መሆኑን ገልጸዋል። በነቀምቴ ከተማ የቀበሌ አራት ነዋሪ አቶ አምሳሉ ገመዳ በበኩላቸው ከዚህ ቀደም ወደ ስታዲዮሙ የሚወስደው መንገድ የተቦረቦረና ጭቃው አስቸጋሪ  እንደነበር አስታውሰው አዲሱ ግንባታ ምቹና ያማረ መሆኑን ተናግረዋል። " የአስፋልት መንገዱ መገንባት አካባቢውን ውብ  አድርጎታል " ያሉት ደግሞ  አቶ ወጋሪ ጫሊ የተባሉ ነዋሪ ናቸው፡፡ የተሰራው የአስፋልት መንገድ በአሁኑ ወቅት 97 በመቶ  የተጠናቀቀው የወለጋ ስታዲዮም  ግንባታ  በሚቀጥለው ዓመት ጨዋታዎችን ማስተናገድ ሲጀምር ተጨማሪ ውበት ያላብሰዋል ተብሏል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም