የኡጋንዳ ካቢኔ ለናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ይሁንታውን ሰጠ

72
ኢዜአ ሀምሌ 4/2011የኡጋንዳ ካቢኔ የአባይ ውሃ ድርሻን ለግብፅና ለሱዳን ብቻ የሚሰጠው የ1929 እና የ1959 የቅኝ ግዛት ስምምነት የሚሽረውን የናይል ተፋሰስ ሃገራት የትብብር ማዕቀፍ ሃሳብ ለማፅደቅ ይሁንታውን እንደቸረ ዴይሊ ሞኒተር ዘግቧል። የኡጋንዳ አካባቢ ሚኒስትር ዶ/ር ጎሬቲ ኪቱቱ የትብብር ማዕቀፉን ማፅደቁ ኡጋንዳን ጨምሮ የላይኞቹ ተፋሰስ ሃገራትን ከአባይ ውሃ ተጠቃሚ ሊያደርጋቸው እንደሚችል ከዴይሊ ሞኒተር ጋር ባደረጉት የስልክ ምልልስ ተናግረዋል። “ካቢኔው በጉዳዩ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ ሃላፊነቱን ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰጥቶታል። የ1929ኙ ስምምነት ለግብፅ መብትን የሰጠና የናይል ውሃን ለመጠቀም የሚያስብ አካል ከግብፅ ይሁንታን መጠየቁ የማይቀር ነበር። አሁን ኡጋንዳ መሬቷን በመስኖ ለማልማት ትፈልጋለች ለዚህም የግብፅን ፈቃድ ማግኘቱ የግድ ሊሆንብን ነበር።” ሲሉ ዶ/ር ኪቱቱ ተናግረዋል። የናይል ተፋሰስ አስር አባል ሃገራትን በውስጡ ያቀፈ ነው። ግብፅ፣ ሱዳን፣ ኢትዮዽያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኡጋንዳ፣ ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ቡሩንዲ፣ ታንዛኒያና ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ሲሆኑ ሃገራቱም የናይል ተፋሰስ ኢኒሺየቲቭ ቋሚ አባላት ናቸው። የቅኝ ግዛት ስምምነቱ 55 በመቶ(55.5 ቢሊዮን ኪውቢክ ሜትር) የሚሆነውን የውሃ ድርሻ ለግብፅ ሲሰጥ 18 በመቶውን (18.5 ቢሊዮን ኪውቢክ ሜትር) ደግሞ ለሱዳን በመስጠት እስከ አሁን እንደዘለቀ ዴይሊ ሞኒተር በዘገባው ማጠቃለያ ላይ አንስቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም