ካምፓኒው በጨርቃጨርቅና አልባሳት ዘርፍ ለመሰማራት ሼዶችን ተረከበ

140
ሐምሌ 4/2011 “ሆፕሉን” የተባለ የሆንግ ኮንግ ካምፓኒ በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፍ ለመሰማራት በባህርዳር ኢንዱስትሪ ፓርክ ትናንት ስምንት ሼዶችን ተረከበ። ካምፓኒው በፓርኩ የመጀመሪያው ምዕራፍ በ75 ሔክታር መሬት ላይ በ250 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነቡት ስምንት  ሼዶች ትናንት በባህርዳር ከተማ የተረከበው የክልልና የፌዴራል ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ነው። የፌደራል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ወይዘሪት ለሊሴ ነሜ በርክክብ  ስነ-ስርዓት ወቅት እንደገለጹት የኢንዱስትሪ ፓርኩ የተገነባው በፌዴራል መንግስት ወጪ ነው። የአማራ ክልል መንግስትና ህዝብ ፓርኩ እዚህ ደረጃ ላይ እንዲደርስ ከፍተኛ ድጋፍ ማድረጋቸውን ያስረዱት ወይዘሪት ለሊሴ የፓርኩን ሁለተኛና ሶስተኛ ምዕራፎች  በፍጥነት ተጠናቅቆ ወደ ስራ እንዲገባ ኮርፖሬሽኑ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል። "የፓርኩ የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ የውጭ ምንዛሬን ከማስገኘት በተጨማሪ ለ6 ሺህ ዜጎች የስራ እድል ይፈጥራል "ብለዋል ። የክልሉ መንግስት የኢንዱስትሪ ፓርኩን በፍጥነት  ወደ ስራ እንዲገባ አስፈላጊ ግብአቶችን በማሟላትና የክልሉን ሰላም በማስጠበቅ በንቃት እየሰራ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ መላኩ አለበል ናቸው። ፓርኩን የክልሉን ህዝብ የስራ አጥነት ጥያቄ ለመመለስ አንድ እርምጃ ወደፊት የሚያራምድና እንደ ሀገር እየገጠመ ያለውን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለመፍታት ትልቅ ድርሻ እንደሚኖረው ገልጸዋል። የባህርዳር ኢንዱስትሪ ፓርክ በ2ሺህ 075 ሄክታር መሬት ላይ የተከለለ ሲሆን በመጀመሪያው ምዕራፍ በ75 ሔክታር መሬት ላይ የሼዶች ግንባታ ተካሔዷል። " በሁለተኛውና ሶስተኛው ምዕራፎች ደግሞ በ2 ሺህ ሔክታር መሬት ላይ ሰፋፊ ግንባታዎች ይካሔዳሉ "ብለዋል ። የ “ሆፕሉን” ካምፓኒ ተወካይ ሚስተር ስቴፋን ስትራንድሉንድ በበኩላቸው  ካምፓኒው ጥቃቅን ስራዎች እየቀሩት  ሸዶችን ለመረከብ የወሰነው የክልሉ መንግስት ለኢንዱስትሪ ፓርኩ መስፋፋት ያለውን ፍላጎት በመገንዘብና የክልሉን የጥሬ እቃ አቅርቦት ዝግጁነት  ከግምት ውስጥ በማስገባት መሆኑን ተናግረዋል። "ካምፓኒው በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ ለመግባት የሰራተኛ ምልመላና ስልጠና ለመስጠት የሚያስችሉት ስራዎች ያከናውናል" ብለዋል ። ካምፓኒው በጨርቃጨርቅና አልባሳት ስራ የካበተ ልምድ እንዳለው አመልክተው  ከአሁን በፊት በቻይና፣ በባንግላዲሽና  በኢንዶኒዥያ መሰል ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል ። በኢትዮጵያም በቅርቡ ወደ ማምረት ለመግባት የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል። በሀገሪቷ ግንባታቸው የተጠናቀቁና እየተገነቡ ያሉትን ጨምሮ 11 ኢንዱስትሪ ፓርኮች እንደሚኖሩ መረጃዎች ያመለክታሉ። ከእነዚህም  ቦሌ ለሚ አንድና ሁለት፣ መቀሌ፣ ሀዋሳ፣ ኮሞቦልቻ፣ ጅማ፣ አዳማና ደብረ ብርሃን ይገኙበታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም