ከአምስት ዓመታት በላይ የቆየው የአፈር መረጃ ካርታ ጥናት ጥቅም ላይ ዋለ

132
ሐምሌ 3 / 2011( ኢዜ አ) ከአምስት ዓመታት በላይ የቆየው የአፈር መረጃ ካርታ ጥናት ጥቅም ላይ መዋሉን የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ አስታወቀ። የግብርና እንቅስቃሴ በሚካሄድባቸው በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ያለውን የአፈር አይነት፣ ውስጣዊ ንጥረ ነገሩንና ባህሪውን በማጥናት ምን አይነት ማዳበሪያ ለምን አይነት አፈር እንደሚያስፈልግ በማሳየት ግብርናን ለማዘመንና በዘርፉ ባለሃብቶችን ለመሳብ ያለመ ነው። የኢትዮጵያ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ከአምስት ዓመታት በላይ በአፈር ምንነት ላይ ሲያጠና የነበረውን ጥናት አስመልክቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እያደረገ ይገኛል። የኤጀንሲው ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ካሊድ ቦምባ በውይይቱ ላይ ጥናቱ ከ95 በመቶ በላይ የግብርና እንቅስቃሴ የሚካሄድባቸው አካባቢዎችን የዳሰሰ መሆኑንና በየክልሉ ይፋ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል። እስካሁን በሰባት ክልሎች የአፈር ጥናት ውጤቱ ይፋ መደረጉንና እስከ መስከረም አጠቃላይ የአገሪቱ የአፈር ጥናት ካርታ ውጤት ለግብርና ሚኒስቴር ይፋ እንደሚደረግ ተናግረዋል። ኢትዮጵያ እስካሁን ትጠቀምባቸው ከነበሩት ዳፕና ዩሪያ የማዳበሪያ አይነቶች በተጨማሪ ሌሎች አምስት ምጥን ማዳበሪያዎች መጠቀም ሲኖርባት ይህም እንደ አፈሩ አይነትና ተፈጥሮ እንደሚለይ ነው በጥናቱ የተረጋገጠው። እስካሁን የነበረው የማዳበሪያ አጠቃቀም የአፈሩን ተፈጥሯዊ ሁኔታ ከግምት ያላስገባና ጥናትን ያልተመረኮዘ ባለመሆኑ አዋጭነቱ ውስን ከመሆኑም ባሻገር ለአንዳንድ የአፈር አይቶነች ተስማሚ እንዳልነበር ተገልጿል። ይህን መሰረት በማድረግ በእያንዳንዱ ወረዳ የጥናቱ ውጤት እንዲደርስ እንደሚደረግና አርሶአደሮች ይህን መረጃ በመጠቀም ምርታማነትን ለማሳደግ ይጠቀሙበታል ነው ያሉት። ጥናቱን መሰረት በማድረግ አንድ የሞሮኮ ኩባንያ በድሬዳዋ ከሶስት ቢሊዮን ዶላር በላይ በሆነ ካፒታል የማዳበሪያ ፋብሪካ ለመገንባት ስራ ጀምሯል ብለዋል። የተለያዩ የውጭ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ለመስራት ፍላጎት እያሳዩ መሆናቸውም ታውቋል። እስካሁን በነበረው እንቅስቃሴ የተለያዩ የአፈር ጥናቶች ቢደረጉም የተደራጀና ተደራሽ የሆነ አሰራር ስላልነበራቸው ለግብርናው ያበረከቱት አስተዋፅኦ አነስተኛ እንደነበር በውይይቱ ተጠቅሷል። በመሆኑም ከአሁን በኋላ የጥናቱን ውጤት በአንድ የመረጃ ቋት ስር በማስቀመጥ ዘመናዊ ግብርናን ለመከተል የሚያስችል ነው ተብሏል። ጥናቱን ለማጥናት ከ10 ሚሊዮን ዶላር በላይ የፈጀ ሲሆን እስከ መስከረም ድረስ ሙሉ የጥናት ውጤቱ ለግብርና ሚኒስቴር የሚረከብ ይሆናል። የአፈር መረጃ ቋቱን የግብርና ሚኒስቴር በባለቤትነት የሚመራው ሲሆን በዘርፉ ጥናት የሚያደርጉ ተቋማት፣ ግለሰቦችና የሚመለከታቸው አካላት በቀላሉ ማግኘት እንደሚችሉ ታውቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም