አየር መንገዱ በበረራ ወቅት በሚሰጠው የምግብ አገልግሎት አሸናፊ ሆነ

82
አዲስ አበባ ሚያዚያ 22/2010 የኢትዮጵያ አየር መንገድ የ2018 የአፍሪካ ምርጥ የምግብ አገልግሎት ሽልማት አሸናፊ ሆነ። ፓክስ ኢንተርናሽናል በጀርመን ሃምቡርግ ባዘጋጀው የሽልማት ስነ-ስርዓት ላይ ነው አየር መንገዱ ምርጥ የተሰኘው። አየር መንገዱ በበረራ ወቅት በሚሰጠው የምግብ መስተንግዶ አገልግሎት የዓመቱ የአፍሪካ ምርጥ ተብሏል። የፓክስ ኢንተርናሽል መጽሔት አሳታሚ አይጃዝ ካሃን እንዳሉት ሽልማቱ በዓመት ሁለት ጊዜ በአንባቢዎች ምርጫ አማካኝነት የሚካሄድ ነው። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም ሽልማቱ በአየር መንገዱ ደንበኞች በተሰጠ ድምጽ መሆኑ ለቀጣይ የተሻለ አገልግሎት አበረታች መሆኑን ጠቁመዋል። በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የተገነባው የምግብ ማቀነባበሪያ በየዕለቱ 100 ሺህ የምግብ ምርቶችን የማዘጋጀት አቅም ሲኖረው በ2025 አየር መንገዱ ያለውን ራዕይ ለማሳካት የሚረዳና የደንበኞችን ፍላጎት የበለጠ ለማርካት የሚያግዝ ነው ብለዋል። በአሁኑ ወቅት የአገር ውስጥን ጨምሮ የቻይና፣ የህንድና የጣልያን ምግቦች እየቀረቡ ሲሆን በቀጣይ የሌሎች አገራት ምግቦችን ለደንበኞች ለማቅረብ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም