አትሌት ደራርቱ ቱሉ በኢጣልያ በተካሄደ ዓለም አቀፍ ሽልማት ዕውቅና ተሰጣት

592
ሐምሌ 2/2011 (ኢዜአ) አትሌት ደራርቱ ቱሉ በኢጣልያ በተካሄደ ዓለም አቀፍ ሽልማት የህይወት ዘመን የስፖርታዊ ጨዋነት ዘርፍ ተሸላሚ ሆነች። ሽልማቱ ኢጣልያ በሚገኝ ''ፕሪሞ ኢንተርናሽናል ፌር ፕሌይ'' በተሰኘ ድርጅት በስፖርቱ  ታሪክ የሰሩ፣ በታማኝነት የተወዳደሩ እና ዘርፉን ያገለገሉና ስፖርትን በማስፋፋት  ታሪክ ለሰሩ ግለሰቦችና ተቋማት እውቅና የሚሰጥበት ነው። በዚህ ዓመት ለ23ኛ ጊዜ ሽልማትና ዕውቅና የተሰጠ ሲሆን ኢትዮጵያዊቷ አትሌት  ደራርቱ ቱሉ ከተሸላሚዎች መካከል ተመርጣለች። አትሌት ደራረቱ ቱሉ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1992 ባርሴሎና በተካሄደ  የኦሎምፒክ ውድድር በ10 ሺህ  ሜትር አሸናፊ በመሆን የመጀመሪዋ አፍሪካዊት ሴት አትሌት ናት። ከዚህ በተጨማሪ በአትሌቲክስ ስፖርት ረጅም ጊዜ በውድድር በቆየችባቸው ዓመታት ናቸው የህይወት ዘመን የስፖርታዊ ጨዋነት እውቅና ያሰጧት። አትሌት ደራርቱ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንን በበላይነት እየመራች ሲሆን የምሥራቅ አፍሪካ አትሌቲክስ የአካባቢው ምክትል ፕሬዚዳንትም ናት። ከአትሌት ደራርቱ ቱሉ በተጨማሪ የቀድሞ የኢጣልያ ቅርጫት ኳስ ተጫዋች አንቶኒዮሪቫ  ተሸላሚ ሆኗል። እንዲሁም የ25 ዓመቷ የሞተር ስፖርት ተወዳዳሪ ኪያራ ፎንታሴ በዚህ እድሜዋ በርካታ ስኬቶችን በማስመዘብ ለወጣቶች አርአያ በመሆን እውቅና ተሰጥቷታል። የስፖርት ማህበራዊ እሴቶችን በማስተዋወቅ ደግሞ ኢጣልያናዊው ማሪዮ ባላታ የእውቅና ሽልማት የተሰጣቸው ሲሆን ሌሎች ስፖርተኞችም ከተለያዩ አገራት እውቅና ተሰጥቷቸዋል። አትሌት ደራርቱ ቱሉ ሽልማቷን በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ቢልልኝ መቆያ አማካኝነት በውክልና መቀበል ችላለች። በአዲስ አበባም ሽልማቷን የተቀበለች ሲሆን ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት አትሌት ገብረእግዚአብሔር   ገብረማርያም እና ከጽህፈት ቤት ኃላፊው አቶ ቢልልኝ መቆያ እጅ  የደረት ላይ የክብር መለያ እና የእውቅና የምስክር ወረቀት ተረክባለች።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም