የሞተር ብስክሌት እገዳው በኑሯቸው ላይ ከፍተኛ ጫና አሳድሯል - የሞተር ብስክሌት አሽከርካሪዎች

78
ሀምሌ 2/2011 ( ኢዜ አ) በአዲስ አበባ ከተማ የሞተር ብስክሌት ማሽከርከር መታገዱ በኑሯቸው ላይ ከፍተኛ ጫና እንዳሳደረ የሞተር ብስክሌት አሽከርካሪዎች ገለጹ። የከተማ አስተዳደሩ በበኩሉ ሞተረኞቹን ወደ ህጋዊ አሰራር የሚያስገባ መመሪያ አዘጋጅቶ በቅርቡ እንደሚተገብር አስታወቋል። የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር በቅርቡ በተሰጠው መግለጫ ከሰኔ 30 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ህጋዊ ያልሆነ የሞተር ብስክሌት በመዲናይቱ እንዳይሽከረከር መከልከሉ ይታወቃል። የሞተር ብስክሌት አሽከርካሪዎች መመሪያው በኑሯቸው ላይ ጫና እንደሚያሳድርባቸው ለኢዜአ ገልጸዋል። በህጋዊ ማዕቀፍ የሚንቀሳቀሱበት መመሪያ እንዲዘጋጅላቸውም ጠይቀዋል። ለሶስት አመታት ሞተር ብስክሌት በማሽከርከር ኑሮውን ሲገፋ የነበረው ወጣት ሚኪያስ እዮብ መመሪያው ኑሮውን ፈታኝ ሊያደርግበት እንደሚችል ስጋቱን ገልጿል። በሞተር ብስክሌት የሚፈጸመውን ዝርፊያ መከላከል የሞተረኞች ድርሻ መሆን እንዳለበት ያስገነዘበው ሰርተው የሚበሉ ሞተረኞች የመመሪያው ሰለባ እንዳይሆኑ የሚያደርግ ህጋዊ አሰራር መዘርጋት እንዳለበት ጠቁሟል። ሞተር ብስክሌትን ለግል ትራንስፖርት መገልገያነት እያዋሉ ያሉት አቶ ደነቀው ማሞ በበኩላቸው "በመዲናይቱ  ከፍኛ የሆነ ትራንስፖርት እጥረት በመኖሩ እገዳው ስራየን በአግባቡ እንዳልከውን አድርጎኛል" ብለዋል። በመሆኑም ወደህጋዊ መስመር የሚገቡበት ምቹ ሁኔታ መፈጠር እንዳለበት ጠይቀዋል። ''ከስደት ይልቅ በአገር ውስጥ ሰርቶ መለውጥን አማራጭ አድርጌ ኑሮዬን እየገፋሁ ባለሁበት ወቅት እንዲህ መደረጉ ድንጋጤን ፈጥሮብኛል'' ሲል የገለጸው ወጣት የታዬ አየነው ሞተረኞች ህጋዊ ሆነው እንዲሰሩ መመቻቸት እንዳለበት ገልጿል። በርካታ ቤተሰቦች በሞተር ሳይክል በመስራት ኑሯቸውን እየደጎሙ እንደሆነ መታወቅ እንዳለበትም አስገንዝቧል። እገዳው ወጣቶች ሰርተው ከመለወጥ ይልቅ ወደ ተለያዩ ወንጀሎች በቀላሉ እንዲገቡ እንደሚያደርግም ጨምሮ ገልጿል። በአዲስ አበባ ከተማ አስስተዳዳር በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ሃላፊ የሆኑት ዶክተር ኢንጂነር ሰለሞን ኪዳኔ በበኩላቸው የሞተር ብስክሌት ማሽከርከር እገዳው ወንጀልን ለመከላከል ብቻ ሲባል ተግባራዊ አለመደረጉን ይናገራሉ። የከተማዋ የትራንስፖርት ፖሊሲ የብዙሃን ትራንስፖርትን የሚያበረታታ በመሆኑና የትራፊክ ፍሰቱ የተሳለጠ እንዲሆን ለማስቻል እንዲሁም እያደገ የመጣውን የሞተር ተሽከርካሪ ቁጥር ሥርዓት ማስያዝ አስፈላጊ መሆኑ እንደታመነበት አስረድተዋል። በመሆኑም የኮድ 2 ሞትር ብስክሌቶች ፈቃድ መሰጠት መቆሙን የጠቀሱት ኃላፊው ከሌሎች የአገሪቱ አካባቢ ከተሞች የሞተር ሰሌዳ ቁጥር እያወጡ የሚመጡ አሸከርካሪዎች ህጋዊነት የሌላቸው በመሆኑ ክልከላ መደረጉን አስታውቀዋል። ህጉ ከሚፈቅድላቸው ውጪ ባላቸው ታርጋ የሚሰሩ የሞተር ብስክሌት አሸከርካሪዎች ወደ ህጋዊነት የሚገቡበት አካሄድ እንደሚፈጠር ጠቁመው ለዚህም መመሪያ መዘጋጀቱንና ችግሩም በዚህ ሳምንት ውስጥ እንደሚፈታ ነው የተናገሩት። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሞተር ብስክሌት እና የከባድ ጭነት ተሽከርካሪዎች መመርያ ማውጣቱ ይታወሳል። መመሪያው የወጣው በከተማዋ ከቀን ወደ ቀን እየተባባሰ የመጣውን የትራፊክ መጨናነቅ እና ፈቃድ የሌላቸው የሞተር ብስክሌቶች መብዛትና ለቁጥጥር አዳጋች በመሆኑ እንደሆነ መገለጹ ይታወቃል። “የሞተር ብስክሌት ፈቃድና ቁጥጥር መመርያ” ከመከላከያ፣ የፀጥታ አስከባሪዎች፣ የድንገተኛ አገልግሎት መስጫ ተቋማት፣ ፖስታ ቤት፣ ኤምባሲዎችና እቃ ከሚያመላልሱ ተቋማት ውጪ የሆኑ ሞተር ብስክሌቶች ከትራንስፖርት ቢሮ ፈቃድ ሳያገኝ ማንኛውም ግለሰብ ሆነ ተቋም ሞተር ብስክሌት በከተማ ውስጥ ማሽከርከር እንደማይቻል ደንግጓል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም