በአዲስ አበባ ሆስፒታሎችንና ትምህርት ቤቶችን የማደስ ስራ ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ ሆስፒታሎችንና ትምህርት ቤቶችን የማደስ ስራ ተጀመረ

ሐምሌ 2/2011 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ የሚገኙ ሆስፒታሎችንና ትምህርት ቤቶችን የማደስ የክረምት በጎ ፍቃድ መርሃ ግብር ዛሬ በይፋ ተጀምሯል። በከተማው የሚገኙ 488 የመንግስት ትምህርት ቤቶችና ሁሉም ሆስፒታሎች እድሳት ይደረግላቸዋል ተብሎ ይጠበቃል። መርሃ ግብሩን የጤና ሚንስትሩ ዶክተር አሚር አማንና የመዲናዋ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልና በጥቁር አንበሳ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመገኘት አስጀምረዋል። በፕሮግራሙ ላይ የተለያዩ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ ባለሃብቶችና ሌሎችም እንግዶች ተገኝተዋል። በዚሁ ጊዜ ኢንጂነር ታከለ ኡማ እንደገለጹት"እድሳት ማለት የመንፈስና የልብ መታደሰ ነው።" በመጪዎቹ ሁለት ወራት ውስጥ በሚካሄደው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ሆስፒታሎች፣ ትምህርት ቤቶችና የመጻዳጃ ቤቶችን በማደስ የህዳሴውን ጉዞ ማረጋገጥ እንደሚቻልም ነው ኢንጅነር ታከለ ኡማ የገለጹት። በሁሉም ትምህርት ቤቶች ይህን የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በመስጠት ውብና ጽዱ እንዲሁም ለተማሪዎች ምቹ የሆነ አካባቢን የማመቻቸት ተግባር በስፋት እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል። ለዚህ መልካም ተግባር መሳካት ባለኃብቶች፣ የተለያዩ ሙያተኞችና ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የበኩሉን መወጣት እንዳለበትም ምክትል ከንቲባው አሳስበዋል። የጤና ሚንስትሩ ዶክተር አሚር አማን በበኩላቸው፤ በአገሪቱ 22 ሚሊየን የሚሆኑ ተማሪዎች በትምህርት ላይ የሚገኙ መሆኑን ገልፀዋል። እነዚህ ተማሪዎች አብዛኛው ጊዚያቸውን የሚያሳልፉት በትምህር ቤቶቻቸው ቅጥር ግቢ ውስጥ በመሆኑ የትምህርት ቤቶቹ አካባቢዎች ፅዱ እንዲሆኑ ይጠበቃል፤ የንጹህ ውሃና የመጸዳጃ አገልግሎትም ሊለቻችላቸው ይገባል ብለዋል። በመሆኑም የትምህርት ቤቶች ንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦትን አስተማማኝ ለማድረግ ይሰራል፤' እስከ 40 ዓመት የሚዘልቅ ንጹህ ውሃን ማቅረብ የሚችል ቴክኖሎጂም ለሁሉም ትምህርት ቤቶች እንደሚዳረሰ የሚደረግ መሆኑን አመልክተዋል።