የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል በቀን ሁለት መቶ ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል የተያዘውን እቅድ ለማሳካት ዝግጅት እያደረገ ነው

72
ሀምሌ 2/2011 ( ኢዜ አ) የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል በአንድ ቀን ሁለት መቶ  ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል በአገር አቀፍ ደረጃ የተያዘውን እቅድ ለማሳካት አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረገ መሆኑ አስታወቀ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ 4 ቢሊዮን የዛፍ ችግኝ የሚተከልበትን ብሔራዊ የአረንጓዴ ልማት ፕሮግራም መርሃ ግብር ግንቦት 18 ቀን 2011 ዓ.ም በአዳማ ከተማ ችግኝ በመትከል በይፋ ማስጀመራቸው ይታወሳል። ይህንንም ተከትሎ በሁሉም ክልሎችና ሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች በስፋት የችግኝ ተከላ ዘመቻ በመካሄድ ላይ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም በአንድ ቀን ውስጥ ሁለት መቶ ሚሊዮን ችግኝ በመትከል በዓለም ሪከርድ ለማስመዝገብ መታቀዱንና ለዚህም ክልልችና ከተማ አስተዳደሮች ከፍተኛ ርብርብ እንዲያደርጉ መጠየቃቸውም ይታወቃል። የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልልም በአገር አቀፍ ደረጃ የተያዘውን ይህን እቅድ ለማሳካት የሚያስችለውን የቅድመ ዝግጅት ስራ እያጠናቀቀ እንደሚገኝ የግብርና ሚኒስቴር ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል። በአንድ ቀን ከሚተከለው 200 ሚሊዮን የዛፍ ችግኝ  የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል ወደ 50 ሚሊዮን ገደማ የሚሆን ችግኝ በከተማና በገጠር ለመትከል አቅዷል። የደቡብ ክልል የእርሻና ተፈጥሮ ኃብት ልማት ቢሮ ም/ ኃላፊ አቶ መለሰ መና በ2011 ዓ.ም ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ከተቋም አሰራር ወጣ ተደርጎ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያሳተፈ አገር አቀፍ ችግኝ የመትከል ስራ እየተከናወነ እንደሆነ ገልጸዋል። ከዚህ ቀደም የተጎዱና የተራቆቱ ቦታዎችን እንዲያገግሙ ለማድረግ ቦታዎቹ ተለይተውና ተከልለው ተስማሚ የሆኑ የዛፍ ችግኞችን የማልማት ስራ በስፋት እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል። በደቡብ ክልል በመንግስት በተለያዩ ተቋማት በተቋቋሙ 7 ሺህ የችግኝ ጣቢያዎች ለበልግና ለመሀር ተከላ የሚሆን 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ የሚሰጡ ችግኞችን ለማዘጋጀት ታቅዶ 667 ሚሊዮን 181 ሺህ 450 ችግኞች መዘጋጀታቸውን ነው አቶ መለሰ ያስረዱት። በዘንድሮው ዓመት የበልግ ዝናብ ቀድሞ በጀመረባቸው የክልሉ አካባቢዎች የችግኝ ተከላ ስራው በትግበራ ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝና እስካሁንም ከ300 ሚሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸውን አመልክተዋል። በክልሉ በችግኝ ተከላው በሁሉም ዞን ሰፊ እንቅስቃሴ እየተደረገ እንደሚገኝና በዚህም አመርቂ ውጤት እየተገኘ መሆኑም ተገልጿል። የከምባታ፣በሲዳማ፣ ጉራጌ፣ ጋሞ፣ ወላይታ እና ስልጤ ዞኖች በችግኝ ተከላው ጥሩ አፈጻጸም ካሳዩ ቦታዎች መካከል በዋነኛነት የሚጠቀሱ ናቸው። የ4 ቢሊዮን የዛፍ ችግኝ ተከላ ብሔራዊ አስተባባሪ ኮሚቴ ሰኔ 29 ቀን 2011 ዓ.ም በሰጠው መግለጫ ግንቦት 18 ቀን 2011 ዓ.ም በተጀመረው መርሃ ግብር እስካሁን ከ 1 ነጥብ 3 ቢሊየን በላይ ችግኝ መተከሉን መግለጹ የሚታወስ ነው። በክረምት ወራት ለመትከል በታቀደው የ4 ቢሊየን ችግኝ ተከላ ዘመቻ ከ4 ነጥብ 7 ቢሊየን በላይ ችግኝና ለችግኝ ተከላው 1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሄክታር መሬት መዘጋጀቱን ኮሚቴው አስታውቋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም