የተሻገርናቸው መከራዎች - የመሻገሩ መፍትሄዎች

135

በሃብታሙ አክሊሉ(ኢዜአ)

ሰሞኑን ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎችን ያጣንበት አሳዛኝ ክስተት አሳልፈናል። መንግስት ድርጊቱን “የመንግስት ግልበጣ” ሙከራ ነው በሚል ነበር የገለፀው። አንዳንድ አካላት ደግሞ ጉዳዩ “የመንግስት” ግልበጣ ሙከራ ሳይሆን የክልል መስተዳድር በሃይል ለመቀየር የተደረገ ጉዳይ አድርገው ሲያራግቡት ሰንብተዋል። ክስተቱ ምንም አይነት ስያሜ ይሰጠው፣ የቱንም አይነት የዳቦ ስም ይውጣለት፣ በየትኛውም ይጠራ… ሃሳብን በሃሳብ የማሸነፍ ድክመታችንን ያጎላ፣ ማጣት የማይገቡን ሰዎችን ያጣንበት ሆኖ ማለፉ ሊያሳዝነንም ሊያሳፍረንም ይገባል። የሆነው ሆኖ በሃገራችን የሚሞከሩ የመንግስት ግልበጣ ሙከራዎችን ተከትሎ ሃገር የምታጣቸው ሰዎች በርካታ አስርት አመታትን ብንለፋ የማናገኛቸው መሆናችንን ስንቶቻችን ልብ ብለን ይሆን?

እኤአ 1960 አብዛኞቹ የአፍሪካ ሃገራት ከቅኝ ግዛት ነፃ የወጡበት አመት ነው። እንግዲህ እነዚህ ሃገራት እምብዛም ከተጠቀሰው አመት ፈቀቅ ሳይሉ ነው የመንግስት ግልበጣ ታሪክን መቋደስ የጀመሩት። አህጉሪቱ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከ200 በላይ የመንግስት ግልበጣ ክስተቶችን አስተናግዳለች። ከሃገራቱም የመጀመሪያውን መፈንቅለ መንግስት ያስተናገደችው ምዕራብ አፍሪካዊቷ ሃገር ቶጎ ነበረች። ጊዜውም እኤአ ጥር 13 ቀን 1963 ነበር። ፈረንጆቹ ‘There is no bad publicity’ እንዲሉ ቶጎ በመንግስት ግልበጣ ክስተት በአፍሪካ የመጀመሪያዋ  ሆና በታሪክ ተቀምጣለች። እስካሁን ከመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ጋር ተያይዞ በአፍሪካ 40 ሃገራት ተፈትነዋል። ለዘመናት የለፉባቸውን ሰዎችንም በነዚሁ ክስተቶች ሳቢያ አጥተዋል። ከነዚህ ሃገራትም ቡርኪናፋሶን ለ10 ጊዜያት የመፈንቅለ መንግስቱ ክስተት ጎብኝቷታል።

እኤአ 1980 ደግሞ በሃገሪቱ 6 የመንግስት ግልበጣ ሙከራዎች ተደርገዋል። በአንድ ወቅት የሃገሪቱ ፕሬዚዳንት የነበሩት ብሌስ ኮምፓዎሬ ሁለት ጊዜ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ማድረጋቸውንም ታሪክ መዝግቦ ይዞታል። እአአ በወርሃ መጋቢት 2012 ላይ በማሊ የተካሄደው የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ለ15ሺ ወታደሮች ሞት እና ከ100 ሺ በላይ ለሆኑ የማሊ ዜጎች መፈናቀል ምክንያት ሆኖ አልፏል። እኤአ በ1971 በኡጋንዳ የተካሄደው መፈንቅለ መንግስት ለ300 ሺ ሰዎች እልቂት ምክንያት የሆነውን የኢዲያሚን ዳዳ መንግስትን ያመጣ ነበር። ተዘርዝሮ የማያልቀውን የአፍሪካ ጉዳይ እዚህ ላይ ገታ እናድርገውና በሀገራችን የተካሄዱ የመንግስት ግልበጣ ሙከራዎችን እና ያደረሱትን ኪሳራ እንመልከት።

 በሃገራችን የመንግስት ግልበጣ ታሪክ የሚጀምረው ወይም ታሪክ በወጉ የመዘገበው በ1921 ዓ.ም አካባቢ አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን የንግስተ ነገስታት ዘውዲቱን መንበር መነቅነቅ ተከትሎ ነው። የንግስቲቷ ወዳጆች የሆኑ ጥቂት የቤተመንግስት ሰዎች በጊዜው ልዑል ራስ ተፈሪ መኮንንን ወደ ስልጣን እንዲመጡ የመፈንቅለ መንግስት ሴራ ያሴሩበት ወቅት ነበር። በጊዜው የአፄ ምኒሊክ አስከሬን ከሚገኝበት በቤተ መንግስቱ ምድር ቤት ውስጥ የነበሩት የንግስቲቷ ወታደሮች በራስ ተፈሪ መኮንን ጦር ከበባ ሲፈፀምባቸው ሌሎች የንግስተ ነገስታት ዘውዲቱ አጃቢ ጦር ደግሞ የራስ ተፈሪን ጦር ከበባ ውስጥ አስገብተው የተፋጠጡበትም ነበር።

ይሁን እንጂ በወቅቱ ካኪ ለባሽ በመባል የሚታወቁት የራስ ተፈሪ ጦር አባላት የንግስቲቷ ጠባቂዎች እንደገና ከበባ ውስጥ አስገብተዋቸው የበላይነትን ሊወስዱ ችለዋል። የተለያዩ የነፍስ ወከፍ መሳሪያዎችን፣ ሽጉጦችን እና መድፎችን የታጠቁት የራስ ተፈሪ ወታደሮች ሁኔታውን በቁጥጥራቸው ስር አድርገው ጉዳዩን በአጭር ቀጭተውታል። ሁኔታው ምንም አይነት የሰው ህይወት አልተከፈለበትም ለማለት አይቻልም። ከከበባ ወደ ከበባ የተሸጋገረ ክስተት ምንም ግጭት አላስተናገደም ለማለት አስቸጋሪ ያደርገዋልና በመፈንቅለ መንግስት ሰበብ የሰው ህይወት ለመገበር ያስገደደ የመጀመሪያው ክስተት ግን ሊባል ይችላል።

ራስ ተፈሪ መኮንን በ1923 ዓ.ም ‘አፄ ሃይለስላሴ ንጉሰ ነገስት ዘ ኢትዮጵያ’ በሚል ስያሜ የንግስና በአላቸውን እንዳከበሩ ብዙም ሳይቆይ ጣሊያን ሃገሪቷን ወረረ። ጀግኖች አርበኞች በዱር በገደሉ ተዋድቀው ከአምስት አመት በኋላ የሃገርን ነፃነት አስከበሩ። በወቅቱም ንጉሱ በስደት በእንግሊዝ ሃገር ቆይተው ሚያዝያ 27 ቀን 1928 ወደ ሃገራቸው ተመለሱ። እዚህ ጋር ታሪኩን በአጭሩ ለማስቀመጥ የታሰበው ከጉዳዩ ጋር ሊያያዝ የሚችል ክስተት ስላለ ነው።  ጃንሆይ በእንግሊዝ ሃገር በስደት በነበሩበት ወቅት ለህዝቡ ተስማሚ የሆነ አስተዳደር ለማምጣት ቃል መግባታቸው እና ወደ ሃገር ቤት ሲመለሱ ወደ ተግባር ይቀይሩታል ተብሎ መጠበቁ ነው። ይሁን እንጂ ንጉሱ ከስደት ወደ ሃገር ቤት ከተመለሱ በኋላ ቃላቸውን ወደ ተግባር ሊለውጡ አልቻሉም።

በጊዜው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ሎሬንዞ ትዕዛዝ  እንግሊዝ ሃገር ቃል የገቡትን ጉዳይ ወደ ተግባር አላመጡትም ሲሉ ጃንሆይን አላስቆም አላስቀምጥ ይሏቸዋል። ጃንሆይ ግን ወይ ፍንክች ይሉ ና በአቋማቸው ይፀናሉ። ሎሬንዞ ትዕዛዝ ከሌሎች አጋሮቻቸው ጋር በመሆን ምክር ያዙ። ይህንን በውል የተረዱት ጃንሆይ ሎሬንዞ ትዕዛዝን በአምባሳደርነት ወደ ሞስኮ ሌሎች ጓደኞቻቸውን ደግሞ ወደ እስር ቤት ወረወሯቸው። ሎሬንዞ ትዕዛዝም ከሞስኮ ወደ ስዊድን በአምባሳደርነት ስም ሲንከራተቱ ኖረው የህይወታቸው ፍፃሜም በባዕድ ሃገር ሊሆን ችሏል። ከአማካሪ አጋሮቻቸው አንዱ የሆኑት ታከለ ወልደሃዋርያት በእስር ከቆዩ በኋላ ንጉሱን ለመግደል ሙከራ አድርገዋል በሚል በተፈፀመባቸው ከበባ ራሳቸው ላይ እርምጃ ወስደዋል። ከዚያም በ1942 ዓ.ም አካባቢ እነ ደጃዝማች ገረሱ ዱኪ፣ እነ ደጃዝማች በዛብህ በመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ሰበብ ህይወታቸውን አጥተዋል። ሃገራችንም የቁርጥ ቀን ልጆቿን በዋዛ አጥታለች።

በተለምዶ ‘የታህሳሱ ግርግር’ ተብሎ የሚጠራውን እና በታህሳስ 04/1953 ዓ.ም በእነ ብርጋዴር ጀኔራል መንግስቱ ንዋይ እና በወንድማቸው ገርማሜ ንዋይ አማካይነት የተካሄደው የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ታሪክ በሰነዱ ካስቀመጣቸው ክስተቶች በዋነኝነት ይጠቀሳል። ይህም የመንግስት ግልበጣ ሙከራ የብርጋዴር ጄኔራል መንግስቱ ንዋይን ጨምሮ የወንድማቸው ገርማሜ ንዋይ እንዲሁም በወቅቱ የደህንነት መስሪያ ቤቱ ሃላፊ የነበሩትን የኮሎኔል ወርቅነህ ገበየሁን የፖሊስ አዛዥ የነበሩትን የጄኔራል ፅጌ ዲቡን ህይወት ቀጥፏል።

ከዚህም በተጨማሪ ብርጋዴር ጄኔራሉ በአንድ ክፍል ውስጥ አግተዋቸው የነበሩ የወቅቱ መከላከያ ሚኒስትር ራስ አበበ አረጋይን ጨምሮ ሌሎች 15 ባለስልጣናትን ከዚህ አለም ላይመለሱ ሸኝቷቸዋል። በዚህ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ሰበብ ከ300 በላይ ሰዎችም ተገድለዋል። ከዚህ ታሪክም የምንረዳው ሃቅ የሃገራችን የመፈንቅለ መንግስት ቅፅበታዊ ክስተት ሃገር በርካታ አስርተ አመታት የለፋችባቸውን የጦር አለቆች እና ምሁራንን ህይወት እንደዋዛ ያጣችበት መሆኑ ነው።

ከዚያ በኋላ የተከሰተው የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ደግሞ በቀድሞ የኢትዮጵያ ጦር ጄኔራሎች አማካይነት ፕሬዚዳንት መንግስቱ ሃይለማርያምን ከስልጣን በሃይል ለማስወገድ ያደረጉትና በግንቦት 08/1981ዓ.ም የተከሰተው ሁኔታ ነው። ይህም የመንግስት ግልበጣ ሙከራ ሃገሪቷ ዳግም ልታገኛቸው የማትችላቸውን እውቅ የጦር መሪዎች አሳጥቷታል። የአየር ኃይል አዛዡ ሜ/ጄነራል አመኃ ደስታ፣ በጊዜው የጦር ሃይሎች ኤታማጆር ሹም የነበሩት ሜጀር ጄኔራል መርዕድ ንጉሴ፣ የመከላከያ ሚኒስትር የነበሩት ኃ/ጊዮርጊስ ሀ/ማርያም፣ የሁለተኛው አብዮታዊ ሰራዊት አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ደምሴ ቡልቶ እንዲሁም የሌሎች ከፍተኛ የጦር ጄኔራሎች ህይወት በመንግስት ግልበጣው ሰበብ ጠፍቷል። ከክስተቱም በኋላ በርካታ ባለስልጣናት በቁጥጥር ስር ውለው የሞት ፍርድ ተፈፃሚ ሆኖባቸዋል።

የቅርቡን ሁላችንም የምናውቀው ነው። የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኤታማጆር ሹም ጄነራል ሰዓረ መኮንንን ጨምሮ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር አምባቸው መኮንን፣ የአማራ ክልል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ አቶ ምግባሩ ከበደ፣  የአማራ ክልል የህዝብ አደረጃጀት ዘርፍ ሃላፊ አቶ እዘዝ ዋሴን እንዲሁም በቅርቡ በጡረታ የተሰናበቱትን ሜጀር ጀኔራል ገዛኢ አበራን ሃገራችን አጥታለች። እንዲሁም ሌሎች የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አባላትን ሰበቡ ላይመለሱ ወስዷቸዋል።  ሃገራዊ ለውጡ እንዲመጣ ምክንያት ከመሆን አልፈው ለውጡ አድጎ ፍሬ እንያፈራ የማድረግ ብቃቱ ያላቸውን ሰዎች ሃገር እንዲሁ በዋዛ አጥታቸዋለች። “የመፈንቅለ መንግስቱ” ተጠርጣሪ ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ፅጌም ቢሆን የያዙት ሃላፊነት ላይ እስኪደርሱ ሃገር የምትከፍለውን ሁሉ ከፍላላቸዋለች፤ ስለሆነም እሳቸውንም አጥተናቸዋል።

ከላይ ለማየት እንደሞከርነው በሃገራችን የሚደረጉ የመንግስት ግልበጣ ሙከራዎች በአብዛኛው የተሳኩ ካለመሆናቸውም በላይ ሃገር ለዘመናት የለፋችባቸውን ጉምቱ ሰዎች ያጣንባቸው ሆኖ ይሰማኛል። ይህም ከየትም የመጣ ወይም ማንም የወለደው ችግር ሳይሆን ለዘመናት ታሞ የቆየው የፖለቲካ ባህላችን ውጤት ነው። በጉዳዮች ዙሪያ ተከራክሮ በመተማመን ለሚመነጭ ሃሳብ ተሸናፊ ላለመሆን የማምለጫ መንገዶችን መጠፋፋት አድርገን ዘመናትን አስቆጥረናል። ፖለቲካችን ለሃሳብ ልዕልና ቦታውን ሳይለቅ አሁን ላይ ደርሰናል።

አሁን ላይ ግን ተነጋግረን እንተማመን፤ ተማምነን በፍቅር ሃገር እንገንባ በምንልበት ወቅት እንኳን ከዚህ ለዘመናት ከተጣባን ችግር ላለመውጣታችን ማሳያ የሆኑ ጥቃቶችን ቅርባችን ላይ ተጋፈጥን። ጉዳዮችን በአመክንዮ እያስማሙ ማቅረብን መቼም ቢሆን አሌ ልንለው አይገባም። የተፈጠረውን መልካም አጋጣሚ በመጠቀምም በጋራ ተነጋግሮ፣ በጋራ በመግባባት ሃገርን ለዘመናት ስትጠራበት ከነበረው ድህነት ማውጣት ሁሉም የሚመለከተው አካል ለአፍታም ችላ የሚለው ጉዳይ መሆን የለበትም። ከላይ ያነሳናቸው ታሪኮችን መልካም መማሪያ በማድረግ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከችግሮቻቸን መቆራረጥ ጊዜ ሊሰጠው አይገባም እንላለን።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም