የጎንደር ዩኒቨርሲቲ 15 አይነት የቆዳ በሽታ የህክምና መድሃኒቶችን በመቀመም ጥቅም ላይ ማዋሉን ገለፀ

130
ጎንደር ሰኔ 3/2010 የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከውጪ ሀገር የሚገቡ 15 አይነት የቆዳ በሽታ የህክምና መድሃኒቶችን በቤተ-ሙከራ በመቀመም ለአገልግሎት እንዲውሉ ማድረጉን አስታወቀ፡፡ ዩኒቨርሲቲው 28ኛውን አመታዊ የማህበረሰብ አገልግሎትና የቴክኖሎጂ ሸግግር አውደ ጥናትና አውደ ራእይ አካሂዷል፡፡ የዩኒቨርሲቲው አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የፋርማሲ ክፍል ዳይሬክተር አቶ ከፍያለው አያሌው ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ሆስፒታሉ በሀገር አቀፍ ደረጃ የመጀመሪያ የሆነውን የመድሃኒት ቅመማ ቤተ-ሙከራ በማደራጀት እየሰራ ነው፡፡ ላለፉት ሶስት አመታትም ምርምርና ፍተሻ የተካሄደባቸው የቆዳ ህክምና መድሃኒቶቹ ፈዋሽነታቸው በቤተ-ሙከራ የተረጋገጠ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ''አለምአቀፍ የህክምና መድሃኒቶች የቅመማ መስፈርቶችን በጠበቀ መንገድ የተዘጋጁት የቆዳ በሽታ የህክምና መድሃኒቶቹ በሆስፒታሉ ህሙማን ላይ ተሞክረው ውጤት ያስገኙ ናቸው'' ብለዋል፡፡ መድሃኒቶች ከውጪ ሀገር የሚገቡ ተመሳሳይ ምርቶችን መተካት የሚችሉና በዋጋ ደረጃም ከውጪ ከሚገቡት መድሃኒቶች ከ200 አስከ 500 ብር የዋጋ ቅናሽ እንዳላቸው ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ የተቀመሙት መድሃኒቶች ለቆዳ ድርቀት መከላከያ፣ ለብጉር፣ ለማድያት፣ ለጸጉርና የእግር ፈንገስ በሽታዎችን ለማከም የሚረዱ መሆናቸውንም አስረድተዋል፡፡ የካንስር ታማሚዎች በቀዶ ህክምና ወቅት የሚሰጣቸውን መድሃኒት የሚተካና የኪንታሮት በሽታን ለማከም የሚረዱ መድሃኒቶችም በቤተ-ሙከራ ደረጃ በፍተሻ ሂደት ላይ እንደሚገኙ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ደሳለኝ መንገሻ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ለቴክኖሎጂ የፈጠራና ምርምር ስራዎች የሚያግዝ ባለ ሰባት ፎቅ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ማእከል አስገንብቶ በቅርቡ ወደ ስራ ለማስገባት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲው የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር መርሻ ጫኔ በዩኒቨርሲቲዎች የሚከናወኑ የምርምር ፕሮጀክቶችን ወደ ተግባር በማሸጋገር በኩል መንግስት ለኢንዱስትሪ ትስስር ትኩረት ሊሰጥ ይገባል ብለዋል፡፡ ባለፉት አመታት ከኢትዮጵያ አእምሮአዊ ንብረት ጽህፈት ቤት ከ10 በላይ የፈጠራ ስራ ቴክኖሎጂዎች የባለቤትነት መብት ዩኒቨርሲቲው ማግኘቱን ምክትል ፕሬዘዳንቱ ተናግረዋል፡፡ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን መስፍን በበኩላቸው በ2010 የበጀት አመት ለ22 የቴክኖሎጂ የፈጠራ ስራዎች ዩኒቨርሲቲው ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ የበጀት ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡ ለሁለት ቀናት የተካሄደው አውደ ጥናትና አውደ ራእይ ‘’ጠንካራና አሳታፊ የማህበረሰብ አገልግሎትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ለዘላቂ እድገት’’ በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀ ነው፡፡ ከተለያዩ የሀገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች የተጋበዙ ምሁራንን ጨምሮ መንግስታዊ አጋር አካላትና የዩኒቨርሲቲው መምህራንና ተማሪዎች ተሳታፊ ሲሆኑ ሶስት ጥናታዊ ጽሁፎችም ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል፡፡ በአውደ ራእዩ በዩኒቨርሲቲው መምህራንና ተማሪዎች የተዘጋጁ የሳይንስና የቴክኖሎጂ የምርምርና የፈጠራ ስራዎችም ለእይታ ቀርበው በተሳታፊዎች ተጎብኝተዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም