በሰለጠኑበት የሙያ መስክ ሀገራቸውን ለመገንባት የበኩላቸውን ጥረት እንደሚያደርጉ በድሬደዋ ተመራቂ ተማሪዎች ተናገሩ

60
ድሬዳዋ ሰኔ 30/2011 ለውጡን በመደገፍ በሰለጠኑበት የሙያ መስክ ተሰማርተው ሀገራቸውን ለመገንባት የበኩላቸውን ጥረት እንደሚያደርጉ አስተያየታቸውን በድሬደዋ ዩንቨርስቲ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የዘንድሮ ተመራቂ ተማሪዎች ተናገሩ፡፡ ከተመራቂ ተማሪዎች መካከል 3 ነጥብ 99 በማምጣት የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚው ተማሪ ሚኒሊክ ንጉሴ ለሀገር ሰላም እና ፍቅር መጠናከር በተሰማራበት የስራ  ቦታ ኃላፊነቱን እንደሚወጣ ገልጿል፡፡ "ሀገር አስተምራናለች ፤ አሁን ደግሞ በየትኛውም መስክ በመሰማራት ሀገራችንን የምንክስበት ጊዜ ነው" ብለዋል፡፡ በሁለተኛ ዲግሪ የተመረቀው አቶ ቤን ሙስጠፋ በበኩሉ በዩነቨርስቲዎች ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲጠናከር ራስን ፣ ቤተሰብን እና ሀገርን ሊመጣ ከሚችል ችግር ማዳን ቅድሚያ የሚሰጠው መሆኑን ተናግሯል። " እኛ ተመራቂ ተማሪዎች በተማርነው ትምህርት ሀገሪቷን የቀድሞ ታላቅነት ለመመለስ የምንችለው  ሀገራችን ሰላም ስትሆን ነው፤ ፣ ሁላችንም የተሻለች ሀገር ለመገንባት በፍቅርና በአንድነት ተባብረን መስራት ይጠበቅብናል"ብለዋል፡፡ ከመከፋፈል በመራቅ ያለውን  መተባበርና ትስስር ጠብቆ የቀሰሙትን  ዕውቀት ለሀገርሰላምና ዕድገት ማዋል እንደሚገባ ያመለከተችው ደግሞ በኢንጂነሪንግ የተመረቀችው  ሄለን ኤሊያስ ናት፡፡ " ባሳለፍነው የትምህርት ዘመን በጎሳና በቋንቋ በመከፋፈል የመማር ማስተማሩ ሂደት ተስተጓጉሏል ፤ይህ ፈፅሞ ዳግም እንዳይከሰት ዩንቨርስቲዎች የሰላም አርአያ መሆን አለባቸው" ብላለች። ሌላው ተመራቂ አብዲ ካፌ" በቀጣይ ሀገር ገንቢና ተረካቢ የሆነው ወጣቶች በሀገሪቱ የተጀመረው  የለውጡ ሂደት ዕውን እንዲሆን በውይይት ለሀሳብ የበላይነት እንዲያብብ እንተጋለን "ብለዋል፡፡ መንግስት በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ለሰላም መጠበቅ መስራት እንዳለበት ያሳሰበው ደግሞ  ተመራቂ አላዘአዛር ተስፋሁን ነው፡፡ አስተያታቸውን የሰጡት ተመራቂ ተማሪዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር  አብይ አህመድ ሰሞኑን በተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡት ሪፖርት ለህግ የበላይነትና ለሰላም ያስተላለፉት መልዕክት ዘገየ ቢሆንም ትክክለኛ እና እንደሚደግፉት ነው የተናገሩት፡፡ ተመራቂዎቹ ለውጡን በመደገፍ በሰለጠኑበት የሙያ መስክ ለሀገር ዘላቂ እድገት የበኩላቸውን ጥረት እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡ ዩኒቨርስቲው ትላንት የክብር ዶክትሬት ዲግሪ የሰጣቸው እና አረጋዊንን በደገፍ በግላቸው የአረጋዊን ማዕከል የገነቡት ወይዘሮ  አሰገደች አስፋው ወጣቶች የሀገር ሰላም እና እድገት ለማስቀጠል ተባብረው እና ተፋቅረው እንዲሰሩ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ ሌላው ክብር ዶክትሬት የተሰጠው  የክብር ዶከተር አርቲስት አሊ መሀመድ ቢራ በሀገሪቱ በትምህርቱም ሆነ በሌሎች ዘርፎች የተገኙ ለውጦች ይበልጥ  እንዲብቡ ተመራቂዎች በፍቅር እና በአንድነት ተባብረው እንዲሰሩ መክሯል፡፡ የድሬደዋ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ያሬድ ማሞ በበኩላቸው " የሁላችንም የሆነችው ኢትዮጵያ የምትለወጠው በኛው በዜጎች በመሆኑ ብዝሀነት አክበረን ለሀገር በአንድነት ልንቆም ይገባል" ብለዋል፡፡ ዩኒቨርስቲው በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን 2ሺህ 880 ተማሪዎች ትናንት በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ አስመርቋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም