ለህዝብ ጥቅምና ለሀገራዊ ለውጡ የታገለው ፋኖ በስሙ ሊነገድበት አይገባም....አቶ ዮሐንስ ቧያለው

194
ሰኔ 30/2011 (ኢዜአ)  ለአማራ ህዝብ ጥቅም መከበርና ለሀገራዊ ለውጡ በጽናት የታጋለው ፋኖ በስሙ ሊነገድበት አይገባም ሲሉ የአዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ገለጹ፡፡ ለአማራ ህዝብ ጥቅም መከበርና ለሀገራዊ ለውጡ በጽናት የታጋለው ፋኖ በስሙ ሊነገድበት አይገባም ሲሉ የአዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ገለጹ፡፡ የአማራ ህዝብ ያነሳቸውን ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ለመመለስ እየተሰራ መሆኑም ተመልክቷል፡፡ የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ዮሐንስ ቧያለው ለኢዜአ እንደገለጹት በመቶ ሺዎችና በሚሊዮን የሚቆጠረው ፋኖ ተደራጅቶ ለአማራ ህዝብ ጥቅምና ነፃነት የታገለና እየታገለ ያለ ወጣት ነው፡፡ “ይህ የተደራጀ ወጣት ኃይል ለክልሉ ልማትና እድገት ፀንቶ እስከታገለ ድረስ ነጻነቱ ይበልጥ ተጠብቆ ትግሉን አጠናክሮ እንዲቀጥል በክልሉ መንግስት በኩል ድጋፍ ይደረግለታል” ብለዋል፡፡ ሀገራዊ ለውጡ እንዲመጣና አሁን ያለበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ በሀገር አቅፍም ሆነ በክልል ደረጃ በዋናነት የጎላ ሚና የተጫወተው ወጣቱ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ “የለውጥ ፍላጎት ካለው፣ ለውጡን አጠናክሮ ከሚያስቀጥልና ከዚሁ ለውጥ ተጠቃሚ ከሚሆን ኃይል ጋር አዴፓ ተባብሮ ይሰራል፤ ድጋፍም ያደርጋል” ብለዋል፡፡ በፋኖ ስም የተደራጀ ወንጀለኛ ፋኖን እንደማይገልጽ አቶ ዮሐንስ ጠቁመው፣ “ወንጀለኛነቱ ሲጋለጥ እኔ ፋኖ ነኝ እያለ ለማምታታት የሚሞክርና ሌላውን ከጎኑ ለማሰለፍ የሚጥር ኃይል ከፋኖ ጋር እኩል ተደምሮ አይታይም” ብለዋል። አቶ ዮሐንስ እንዳሉት ባለፈው ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም በባህር ዳር ከተማ በተፈጸመ የከፍተኛ አመራሮች ግድያ በጣት የሚቆጠሩ ቡድኖች በወንጀሉ በግልፅ ተሳትፈዋል። ከእነዚህ ውስጥ አንዳንዶች ወንጀሉን አምነው እጃቸውን ሲሰጡ ሌሎች ደግሞ በፈጸሙት ወንጀል እየተሸበሩ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ “አዴፓ ከፋኖ ጋር ወይም የፋኖ ትክክለኛ አስተሳሰብ ካለው ወጣት ጋር ግብ ግብ ሊገጥም አይችልም ” ያሉት ኃላፊው፣ “ትግሉ ወንጀለኛን ከማያዝ አንፃር መሆኑን ህብረተሰቡ ሊረዳ ይገባል” ብለዋል፡፡ “በተደራጀ መንገድ የመንግስትን እጅ ለመጠምዘዝና የህብረተሰቡን ሰላም በማወክ በወንጀል የሚሳተፉ ካሉ የገዥውን ፓርቲ ጨምሮ የማንም ፓርቲ፣ ቡድንና ድርጅት አባል ቢሆኑም ከተጠያቂነት አያማልጡም” ብለዋል፡፡ ፋኖ በስሙ መነገጃ ሊሆን እንደማይገባ የጠቆሙት አቶ ዮሐንስ የፋኖን ስም ይዘው በወንጀል የሚሳተፍ ግለሰብም ሆነ ቡድንን የአማራ ወጣት ሆነ ህብረተሰቡ አምርሮ ሊታገላቸው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ በባህር ዳር ከተማ የተፈጠረውን ችግር ለማረጋጋትና በወንጀሉ የተሳተፉ አካላትን ለህግ ለማቅረብ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከክልሉ የፀጥታ ኃይል ጋር በመተባበር እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የመከላከያ ሠራዊቱ በክልሉ ጥያቄ ድጋፍ ለመስጠት ወደክልሉ የገባ ከመሆኑም በላይ በሰላምና መረጋጋቱ የክልሉ መንግስት በሚሰጠው አቅጣጫ ብቻ እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል። ይሁን እንጂ ወንጀለኞች የክልሉን የፀጥታ መዋቅር ለመከፋፈል እንደሞከሩት ሁሉ የፌደራሉን ሠራዊት የከበረ ስሙን ለማጠልሸት የሚደረገው ሙከራ ከወንጀሉ ለማምለጥ የሚደረግ አንዱ የሴራና የተንኮል ሂደት መሆኑን አቶ ዮሐንስ ገልጸዋል፡፡ “በመሆኑም ህብረተሰቡ የዚህ ዓይነትን የተንኮል አካሄድን በመረዳት ሠራዊቱ የሰላምና መረጋጋቱ ሂደት አንድ አካል መሆኑን ሊረዳ ይገባል” ብለዋል። አዴፓ የአማራ ክልል ህዝብ በተደጋጋሚ የሚያነሳቸውን መሰረታዊ ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ለመፍታት በጠቅላላ ጉባኤ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት እየሰራ መሆኑንም አቶ ዮሐንስ አስታውቀዋል፡፡ በተለይም የወሰንና የህገ መንግስት ይሻሻል እንዲሁም በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ አጀንዳ ተይዞ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ “አሁን በክልሉ ሰላማዊ ሁኔታ እየተፈጠረ ነው ያሉት” ኃላፊው ህብረተሰቡ የአካባቢውን ሰላምና ደህንነት ከመጠበቅ ባለፈ ውዥንብር ከሚፈጥሩና የተዛባ በረጃ ከሚሰጡ የብዙሀን መገናኛዎች እራሱን መጠበቅ እንዳለበት አሳስበዋል። በሁሉም የልማት መስኮች ንቁ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆንም አስገንዝበዋል፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም