የሰላም እንቅፋቶችን ለማጋለጥና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ነዋሪዎች ገለጹ

70
ፍቼ እና አምቦ ሰኔ 3ዐ/2ዐ11 የሰላም እንቅፋቶችን ለማጋለጥና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት በመደገፍ የድርሻቸውን እንደሚወጡ በኦሮሚያ ሰሜንና ምዕራብ ሸዋ ዞኖች ነዋሪዎች ገለጹ። ነዋሪዎቹ ድጋፋቸውን የገለጹት በየአካባቢያቸው ዛሬ ባካሄዱት ሰላማዊ ሰልፍና ኮንፍረንስ ነው። በሸዋ ዞን ኩዩና ደገም ወረዳዎች  የሚገኙ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ለሰላምና ልማት እንቅፋት የሆኑ ኃይሎችን እንደሚያወግዙ ባካሄዱት ሰልፍ አስታውቀዋል፡፡ በተለይ “ አባዎ ሸኔ ” በሚል  በኦሮሞ ስም ተደራጅቶ እኩይ ተግባሮችን በመፈፀም ላይ ያለው ቡድን እንደማይወክላቸው ገልጸዋል፡፡ በኦሮሞ  ሥም የፖለቲካ ትርፍ ማግኘት አይቻልም፣ ኦሮሞ የቆየው ባሕሉ አንድነት ፣ ፍቅርና ሰላም ነው፣ የሰው ሕይወትና ንብረት እያጠፉ ለኦሮሞ እንታገላለን ማለት ጊዜው ያለፈበት ማታለያ ነው   የሚሉ  መፈክሮች ነዋሪዎቹ በሰልፉ ላይ  አስተጋብተዋል። ከነዋሪዎቹ መካከል  አቶ አብዲሣ ኦቦማ የአካባቢያቸውን ሰላም በማወክ በርካቶችን ላልተገባ ጉዳትና ጭንቀት እየዳረገ ያለውን አባዎ ሸኔ የተባለውን የታጠቀ ኃይል መንግስት ስርዓት እንዲያሲይዝላቸው ጠይቀዋል። አርሶ አደር ነገዎ ቄሬንሣ በበኩላቸው ለኦሮሞ መብት ቆሜያለሁ በሚል የአርሶ አደሮችን ንብረት በመንጠቅ  ልጆቻቸውን ለትጥቅ ትግል ይፈለጋሉ በማለት የሚነጥቃቸውን አባዎ ሸኔ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ይኸን አፍራሽ ተግባር ለማስቆም መንግስት ለሚያደርገው ጥረት በመደግፍ የድርሻቸውን እንደሚወጡ  ገልፀዋል፡፡ በንግድ ሥራ የሚተዳደሩት አቶ ረሻድ አብደታ የነፍስ ግድያና የንብረት ዘረፋ እየፈፀሙ ለህዝብ ቆሜያለሁ ማለት ሕዝብን መናቅ በመሆኑ መንግስት በአጥፊዎች ሕጋዊ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል፡፡ የተጀመረው የለውጥና የልማት እንቅስቃሴ ለማደናቀፍ የሚሯሯጡ አፍራሽ ኃይሎች ተጋልጠው  ለህግ  እንዲቀርቡ የበኩላቸውን ድጋፍ እንደሚሰጡ ተናግረዋል፡፡ በወረዳዎቹ በተካሄደው ሕዝባዊ ሰልፍ ላይ የተገኙት የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ እንደሻው ብርሃኑ ሕዝቡ ፊቱን ወደ ልማትና ሀገራዊ ለውጥ በማዞር ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ጥሬት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል። በዚህ ሂደት  ለኦሮሞ ቆሜያለሁ በሚል የተሳሳተ አካሄድ ሕይወት ማጥፋትና ንብረት ማውደም የሚያሳዝን በመሆኑ ነዋሪዎች ይኸን ለማክሸፍ ከመንግስት ጐን ተሰልፈው እያደረጉ ያለውን ጥረት አጠናክረው እንዲቀጥሉ አስገንዝበዋል። መንግስትና የፀጥታ ኃይሉም አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግ ለሕግ የበላይነት፣ ለሰላም መስፈን እርምጃ እንደሚወስዱ አመልክተዋል፡፡ ህብረተሰቡ ለተጀመረው ሀገራዊ ለውጥና አረንጓዴ ልማት መሳከት ድጋፋቸው እንዲቀጥሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ በሰልፉ የመንግስት ሰራተኞች፣ አርሶ አደሮችና ነጋዴዎች ጨምሮ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ከምዕራብ ሸዋ ዞን የተወጣጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ዛሬበአምቦ ከተማ የሰላም  ኮንፈረንስ በካሄዱበት ወቅት የጸጥታ ችግሮች በመፍታት የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ከመንግስት ጎን እንደሚቆሙ ገልጸዋል። ከኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች መካከል የግንደበረት ወረዳ ነዋሪ አቶ ምትኩ ፌዬ መንግስት የህግ በላይነትን በማስከበር ከምንግዜውም በላይ የህዝቡን ሰላምና ደህንነት ማስጠበቅ እንዳለበት አመልክተዋል። መንግስት  የፀጥታ ችግሮችን በመፍታትና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በሚደርገውን ጥረት በመደገፍ የበኩላቸውን እንደሚወጡም ተናግራል፡፡ የአካባቢያቸው ሰላም ለማስጠበቅና ልማትን ለማጠናከር የድርሻቸውን አስተዋጽኦ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ የጮቢ ወረዳ ነዋሪ አቶ ጫልቺሳ ፉላሳ  ናቸው፡፡ "ሰላም ከሌለ ምንም ነገር መስራት አይቻልም፣ ወጥተው መግባት፣በልማት ላይ መሳተፍ አይቻልም ብለዋል። መንግስት አሁን እያሳየ ያለውን ትዕግስቱን በመተው የህግ የበላይነትን በማስከበር ሰላምና ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነት በአግባቡ ሊወጣ እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡ ኮንፈረንሱን የመሩት የዞኑ  ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገላና ኑረሳ ህዝቡ በከፈለው መስዕዋትነት የተገኘውን ለውጥ ወደ ኋላ ለመመለስ የሚጥሩ ኦነግ ሸኔ ብለው እራሳቸውን የሚጠሩትን ቡድኖች ለማስቆም  መንግስት እያደረገ ያለውን ህብረተሰቡ ጥረት እንዲደግፍ ጠይቀዋል። የኦዲፒ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ ሰለሞን መኮንን በበኩላቸው ኮንፍረንሱ ሀገራዊ ለውጡን ለማደናቀፍ የሚደረጉ የጥፋት ሙከራዎችን ለማጋለጥና ህብረተሰቡ የሚያደርገውን ሁለንተናዊ ድጋፍ ለማጠናከር ጉልህ ድርሻ እንዳለው ተናግረዋል። አቶ ሰለሞን እንዳሉት በዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች ውስጥ በመዘዋወር በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት የሚደርሱትን ሽፍቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ እጅ እንዲሰጡ ድጋፉን  ማጠናከር አለበት፡፡ ኮንፈረንሱ በክልሉ የህግ የበላይነትን በማስከበር በኩል ያገጠሙ ፈተናዎችና ቀጣይ ስራዎች ላይ ያተኮረ ባለ ሰባት ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቋል፡፡ ለአንድ ቀን በተካሄደው ኮንፍረንሱ ከዞኑ 22 ወረዳዎች የተወከሉ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም