ሰመራ ዩኒቨርሲቲ በአርብቶ አደር ልማት የልህቀት ማዕከል ሆኖ እንዲያገለግል ተጠየቀ

141
ሰኔ 30/2011 ሰመራ ዩኒቨርሲቲ በአርብቶ አደር ልማት የልህቀት ማዕከል ሆኖ እንዲያገለግል የአፋር ክልላዊ መንግስት ጠየቀ። የክልሉ መንግስት ጥያቄ በቅርቡ እየተሻሻለ ባለው የትምህርት ፍኖተ ካርታ ላይ መልስ እንዲያገኝ እንደሚደረግ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትሯ ፕሮፌሰር ሒሩት ወልደማርያም አስታውቀዋል። ትናንት በዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች ምረቃ ስነስርአት ላይ የተገኙት የክልሉ ምክትል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ ኡስማን መሃመድ እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው ስራ ከጀመረ ግዜ አንስቶ ለክልሉ ልማት የድርሻውን እየተወጣ ነው። በሰው ሃብት ልማት፣ በጥናትና ምርም እንዲሁም በማህብረሰብ አገልግሎቶች እያደረገ ያለውን ተሳትፎን በማሳያነት ጠቅሰዋል። ከአገሪቱ የቆዳ ስፋት 60 በመቶ የሚሆነውንና ወደ 14 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ የያዘውን እንዲሁም ከፍተኛ የእንስሳትና እምቅ የተፈጥሮ ሃብት ባለቤት ለሆነው አርብቶ አደር ህብረተሰብ ልማት መንግስት የፖሊሲና የህግ ማዕቀፎችን አዘጋጅቶ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል። ይሁንና የመንግስትን ጥረት በመደገፍ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እያበረከቱት ያለው ተሳትፎ በሚፈለገው ልክ አለመሆኑንና ውስንነት እንዳለበት ተናግረዋል። የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚነስቴር በቅርቡ የትምህርት ፍኖተ ካርታን ለማሻሻል እያዳረገ ባለው ጥረት ይህን ታሳቢ እንዲያደርግ አመልክተዋል። ሚኒስቴር መስሪያቤቱ በማስተካከያ እርምጃው የሰመራ ዩኒቨርሲቲ የአርብቶ አደሩን የኑሮ ዘይቤ ሊያሻሽሉና ሊያግዙ የሚችሉ የቴክኖሎጂና የምርምር ውጤቶች የሚወጡበት የልህቀት ማዕከል እንዲሆንም  ጠይቀዋል። የአርብቶ አደሩን ኑሮ በሚለውጡ ተጨባጭ ሥራዎች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባም ነው የተናገሩት። የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትሯ ፕሮፌሰር ሒሩት ወልደማርያም በበኩላቸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እንደአዲስ ከተደራጀ በኋላ በከፍተኛ ትምህርት ጥራትና ተደራሽነት ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለመሙላት የተቀናጀ ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅትም በተዘጋጀው አዲስ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ላይ ከተለያዩ አካላት የተነሱ ጠቃሚ ግብአቶችን ያካተቱ የመፍትሄ እርምጃዎች መውሰድ መጀመራቸውን ጠቁመዋል። ለእዚህም በተመራቂዎች ላይ የሚስተዋለውን የእውቀት፣ የክህሎት እንዲሁም የስነ-ምግባር ክፍተት ለመሙላት የሚያስችሉ አዳዲስ የትምህርት አይነቶች ያካተተ ሰርአተ-ትምህርት እየተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል። የክልሉ መንግስት ሰመራ ዩኒቨርሲቲ የአርብቶ አደር ልማት የልህቀት ማዕከል እንዲሆን ያቀረበው ጥያቄ ተገቢና ትክክለኛ መሆኑን የገለጹት ሞኒስትሯ እየተሻሻለ ባለው የትምህርት ኖኖተ-ካርታ ላይ በቅርቡ መልስ አንደሚሰጠው ተናግረዋል። እንደ እርሳቸው ገለጻ በአድሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ዝግጅት መሰረት ዩኒቨርሲቲዎች በሚገኙባቸው የልማት ኮሪደሮችና ባላቸው ሰብአዊና ቁሳዊ ሀብት ከአካባቢያዊ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ተቃኝተው እንዲደራጁ የማድረጉ ስራ ቅድሚያ ተሰጥቶታል። ሰመራ ዩኒቨርሲቲም በአርብቶ አደር ልማት ድንበር ተሸጋሪ የምርምርና የትምህርት መርሀግብሮች  በቅሪተአካልና ተያያዥ ጉዳዩች ላይ ትኩረት ሰጥቶ ቢሰራ ከሀገር አቀፍ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፍ ጭምር ተወዳዳሪ መሆን እንዲሚችልም ሚኒስትሯ አስታውቀዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም