በትግራይ አለአግባብ የተከፈለና ያልተሰበሰበ የመንግስት ገንዘብ በሂሳብ ምርመራ ተገኘ

90
ሰኔ 30/2011በትግራይ ክልል አለአግባብ የተከፈለና ከባለሀብቶች የመሬት ኪራይ ያልተሰበሰበ ከ49 ሚሊዮን ብር በላይ በሂሳብ ምርመራ መገኘቱ ተገለጸ። ሶስተኛ ቀኑን በያዘው የትግራይ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት  16ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ የክልሉ ዋና ኦዲተር ኃላፊ ዶክተር ረዳኢ በርሄ   በ16 የመንግስት ተቋማት የተካሄደውን የኦዲት ስራ  ሪፖርት አቅርበዋል ። ኃላፊው ለምክር ቤቱ ካቀረቧቸው የተቋማት ሪፖርት መካከል  የዓዲግራት ማዘጋጃ ቤት ይገኝበታል፡፡ በማዘጋጃ ቤቱ በ2011 የበጀት ዓመት  ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ የመንግስት ገንዘብ ከካሳ ክፍያ ጋር በተያያዘ ያለአግባብ ለግለሰቦች እንዲከፈል ማድረጉን በኦዲት ግኝት መረጋገጡን አስታውቀዋል። የካሳ ኮሚቴ ሳያጣራውና ለአንድ ቦታ ሁለት ጊዜ ካሳ የተከፈለበት፣ ካሳ ለማይገባቸውና በከፊል ለሚነሱ አለአግባብ የተከፈለ ካሳ መኖሩ ጠቅሰዋል። በሌላ በኩል ደግሞ በዚሁ የበጀት ዓመት  በቃፍታ ሑመራ ከ250 በላይ ባለሃብቶች የመሬት ኪራይ ውል መክፈል ሳይችሉ የእርሻ ስራቸውን እያከናወኑ መሆናቸውን ዶክተር ረዳኢ ገልጸዋል። በዚህም ከ39 ሚሊዮን ብር በላይ መንግስት ማግኘት የሚገባው ገንዘብ በወቅቱ መሰብሰብ እንዳልተቻለ ለምክር ቤቱ ባቀረቡት የኦዲት ግኝት ሪፖርት ላይ   አመላክተዋል። ኃላፊው በማያያዝም  የትግራይ ክልል ቤቶች ኤጀንሲ ባለፉት ሶስት ዓመታት ያገለገሉ ንብረቶች እንዲወገዱ በማድረግ ከ40 ሚልዮን ብር በላይ ለመንግስት ገቢ ማድረጉን ጠቅሰዋል። የኦዲት ግኝቱን መሰረት በማድረግ የምክር ቤቱ በጀትና ኦዲት ቋሚ ኮሚቴ  እርምጃ እንዲወሰድ ክትትላቸውን ማጠናከር እንደሚጠበቅባቸውም ተመልክቷል። የክልሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ዶክተር ፋና ሓጎስ በበኩላቸው ባቀረቡት ሪፖርት ህብረተሰቡ ጉዳዮችን በባህላዊ እርቅ ለመፍታት የሚያደርገው ጥረት አነስተኛ እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል። ይህም በፍርድ ቤት ስራ ላይ ጫና እየፈጠረ መሆኑን አስረድተዋል። በ2003 ዓ.ም  ወደ ፍርድ ቤቶች የቀረቡ መዝገቦች ቁጥር 118 ሺህ እንደነበሩና ዘንድሮ ወደ 204 ሺህ ከፍ ማለቱን በማነፃፀር ባለፉት አስር  ዓመታት ጫናው እየበረታ መምጣቱን አመላክተዋል። ዘንድሮ ወደ ፍርድ ቤቶች ከቀረቡት መዛግብት ውስጥ 179 ሺህ መዝገቦች ውሳኔ ማግኘታቸውን ገልፀዋል።ወደ ፍርድ ቤቶች የሚቀርቡ መዛግብት የቆይታ ጊዜቸውን ለማሳጠር ጥረት እየተደረገ መሆኑን ያስረዱት   ዶክተር ፋና ዘንድሮ ውሳኔ ካገኙት መዛግብት መካከል ግማሽ ያህሉ የቆይታ ጊዜቸው ከስድስት ወራት በታች መሆኑን ጠቁመዋል። ምክር ቤቱ በሁለቱም ተቋማት በቀረቡት ሪፖርቶች ላይ ከተወያየ በኋላ ትናንት ማምሻውኑ አፅድቋቸዋል ።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም