የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ 6 ሺህ 824 ተማሪዎችን አስመረቀ

103
ሰኔ 30/2011 የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በ42 የትምህርት ዘርፎች በመደበኛና በተከታታይ መርሃ ግብር ያስተማራቸውን 6 ሺህ 824 ተማሪዎችን ዛሬ አስመርቋል። በመጀመሪያ፣ በማስተርስና በዶክትሬት ዲግሪ ከተመረቁት አጠቃላይ ተማሪዎች መካከል 180 የሚሆኑት ከደቡብ ሱዳን፣ ሶማሌላንድ፣ ሶማሊያና የመጡ ናቸው። እነዚህ የውጭ ዜጎች በዩኒቨርስቲው የተማሩት የኢትዮጵያ መንግስት በሰጠው ነጻ የትምህርት እድል አማካኝነት ነው። በምረቃው ላይ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ፍቅሬ ደሳለኝ ዩኒቨርሲቲው ትኩረቱን በሶስተኛ ዲግሪ ትምህርት ላይ በማድረግ ዘንድሮ 29 ተማሪዎችን በዶክትሬት ዲግሪ ማስመረቁን ተናግረዋል። ዩኒቨርሲቲው የአንድ ፓርቲ አገልጋይ ነው የሚለውን አስተሳሰብ ለመቀየር በርካታ የገጽታ ግንባታ ታገባራት መከናወናቸውንም ጠቅሰው ዩኒቨርሲቲው ለሁሉም ዜጎች ክፍት የሆነ የምሁራን መፍለቂያ አምባና የእውቀት ማዕከል ለማድረግ በትኩረት እየሰራን ነው ብለዋል። ዩኒቨርሲቲው ተቋቁሞ ሥራ ላይ በቆየባቸው ባለፉት 25 ዓመታት ከዲፕሎማ አንስቶ እስከ ሶስተኛ ዲግሪ የትምህርት ደረጃዎች ከ35 ሺህ በላይ ተማሪዎችን አስመርቋል። በአሁኑ ወቅት ትኩረቱን በድህረ ምረቃ ፕሮግራም ላይ ያደረገው የሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ የቅበላ አቅሙን በማሳደግ በስድስት የትምህርት ዘርፎች በዶክትሬት ደረጃ ትምህርት እየሰጠ ይገኛል። ዘንድሮ ከተመረቁት መካከል በ25 የእውቀት ዘርፎች በሁለተኛ ዲግሪ እና በቅድመ ምረቃ ደግሞ በ11 ዘርፎች ትምህርታቸውን የተከታተሉ ይገኙበታል። በምረቃው ስነ-ስርዓት ላይ የተገኙት የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር በዛብህ ገብረእየሱስ እንዳሉት መንግስት የጀመረውን አካባቢን የመንከባከብ ተግባር በጋራ እውን በማድረግ ኢትዮጵያን ለአሁኑና ለመጪው ትውልድ ምቹ የመኖሪያ ስፍራ መፍጠር ይጠበቅባቸዋል። ተማራቂ ተማሪዎችም አገራቸውን ወደፊት ለማራመድ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ አሳስበዋል። መንግስት በተለይ በመጪው ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓም 200 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል የያዘውን እቅድ ለማሳካት ተመራቂዎች የአካባቢያቸውንና የዩኒቨርሲቲውን ማህበረሰብ በማስተባበር ችግኝ እንዲተክሉ ጥሪ አቅርበዋል። የሚተከሉት ችግኞችም የምርቃታችሁ ማስታወሻ ይሆናሉ ሲሉም አክለዋል። በሁለተኛ ዲግሪ ትምህርቱን የፈጸመው ተስፋዬ አባተ በተመረቀበት ሙያ አገሩን ለማገልገል ቁርጠኛ መሆኑን ተናግሮ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የቀረበውን የችግኝ ተከላ ጥሪ በመቀበል ሃላፊነቱን እንደሚወጣ ገልጿል። "ከዚህም ባለፈ በክረምት በበጎ ምግባር አገልግሎት ላይ በመሰማራት የሚጠበቅብኝን አስተዋጽኦ አበረክታለሁ" ብሏል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም