ለአፍሪካውያን የእለት ተዕለት ኑሮ መለወጥ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል- የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር

53
ካምፓላ ሰኔ 3/2010 በአፍሪካ እየተመዘገበ ያለውን ኢኮኖሚያዊ ለውጥ የዜጎችን የእለት ተዕለት ኑሮ መለወጥ በሚያስችል መልኩ ማስኬድ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ተናገሩ። ጠቅላይ ሚነስትር አብይ በ29ኛው የኡጋንዳ ብሄራዊ የጀግኖች በዓል ላይ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል። በዕለቱም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ለአገራቸው፣ ለቀጠናውና ለአፍሪካ ነጻነት ባደረጉት አስተዋጽኦ የኡጋንዳ ከፍተኛ ሜዳሊያ ከአገሪቷ ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ተበርክቶላቸዋል። ዶክተር ዐቢይ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት አፍሪካ በግልጽ የሚታይ ከፍተኛ እድገት እያስመዘገበች በመምጣቷ የአለምን ትኩረት ስቧል፡፡ እድገቱን አፍሪካን ከዓለም ኢኮኖሚ ጋር ሊያስተሳስራት በሚችል ደረጃ በመቀየር የዜጎችን የእለት ተዕለት ኑሮ መለወጥ እንደሚገባም ተናግረዋል። እንደ ዶክተር አብይ ገለጻ፣ አገሮቹ ቅድሚያ የሚሰጡትን  ነገር መለየት ይኖርባቸዋል። ከአጋሮች ዘንድ  አቅምን ለመገንባት የሚያስችል ድጋፍ ለማግኘት መጣርም ያስፈልጋል። የአፍሪካን ፍላጎት ማሳካት የሚያስችል ፖሊሲ ለመቅረጽ፣ ለራስ በተስማማ መንገድ ለመቅዳትና የውስጥ ጥንካሬ ለመፍጠር ድጋፉ አስፈላጊ ነውም ብለዋል። የአፍሪካን ልማት ለማፋጠንና ተግባር አቀፍ ድጋፍ ለማግኘት በቀጠናም ሆነ በዓለምአቀፍ ደረጃ የጋራ መግባባትን መገንባት ተገቢ መሆኑን አጽንኦት ሰጠውታል። አፍሪካ ለቀረጸችው አጀንዳ 2063 ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ መሆን ጠንክሮ መስራት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ያመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣  በተለይም በመጀመሪያው አስር ዓመት ጊዜ ውስጥ ለስትራቴጂና የተግባር እንቅስቃሴ መስራት አስፈላጊ መሆኑን አመልክተዋል። ከዚህ አኳያም ኢትዮጵያ ከኡጋንዳ ጋር ያላትን ትብብር የበለጠ ለማጠናከር ዝግጁነቷን ያረጋገጡት ዶክተር ዐቢይ የሁለቱን አገሮች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ይበልጥ ለማጎልበት የባህል፣ የትምህርትና የንግድ ልውውጥን ማሳደግ እንደሚገባም ተናግረዋል። መንግስት የሁለትዮሽ፣ የአካባቢና የዓለምአቀፍ ትብብርን ለማጠናከር ያለውን ጽኑ ፍላጎት ያመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የኡጋንዳ መንግስትና ህዝብ እስከዛሬ ያስመዘገቡትን ስኬት አጠናክሮ ለማስቀጠል ሰላማቸውን መጠበቅ እንዳለባቸው መክረዋል። ባለፉት አስርት ዓመታት ኡጋንዳ ያስመዘገበችው እድገት ለህይወታቸው ሳይሳሱ በተሰዉ ልጆቿ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ እነርሱ ክቡር ህይወታቸውን ለአገራቸው አሳልፈው ባይሰጡ ውጤት ማስመዝገብ፣ ሰላምና መረጋጋትን ማረጋገጥ አይቻልም ብለዋል። በመጀመሪያው ቀን ሁለቱ መሪዎች ባደረጉት የሁለትዮሽ ውይይት በትምህርት፣ በግብርና፣ በውሃና አካባቢ፣ በኃይል አቅርቦት፣ በንግድ፣ በቱሪዝምና ኢንቨስትመንት፣ በትራስፖርትና ኮምዩኒኬሽን፣ በመከላከያ፣ በባህልና ስፖርት ላይ ያላቸውን ትብብር የበለጠ ለማሳደግ ተስማምተዋል። መሪዎቹ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን የንግድ ልውውጥ መጠን የማሳደግ አስፈላጊነት ላይም በአጽንኦት ለመስራት ተስማምተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የኡጋንዳ ይፋዊ የስራ ጉብኝታቸውን አጠናቀው ትናንት ምሽት  ግብጽ የገቡ ሲሆን ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አልሲሲ አቀባበል አድርገውላቸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም