በዩኒቨርሲቲው ያዳበርናቸውን የመቻቻል፣ የአንድነትና የፍቅር እሴቶች በማጎልበት ለሰላም እንሰራለን...የወሎ ዩኒቨርሲቲ ምሩቃን

125
ሰኔ 29/2011 በዩኒቨርሲቲው ያዳበርናቸውን የመቻቻል፣ የአንድነትና የፍቅር እሴቶች በማጎልበት ለአካባቢያችን ሰላም የድርሻችንን እንወጣለን ሲሉ የወሎ ዩኒቨርሲቲ ምሩቃን ተማሪዎች ተናገሩ፡፡ በዩኒቨርሲቲው የኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ በተለያዩ የትምህረት መርሀ ግብሮች ያሰለጠናቸውን 1ሺህ13 ተማሪዎችን ዛሬ አስመርቋል፡፡ በዚህ ወቅት ከሴቶች አጠቃላይ ውጤት 3 ነጥብ 83 በማምጣት የሜዳሊያ የተሸለመችው ተማሪ ትግስት ዘለቀ በዩኒቨርሲቲ ቆይታዋ መቻቻል፣ አብሮነት፣ አንድነትንና ፍቅርን መማሯን ተናግራለች፡፡ የወሎ ህዝብ ለሌሎች ምሳሌ የሚሆን የእንግዳ ተቀባይና ሁሉንም እኩል የማክብር ባህል ስላለው በአራት ዓመት ቆይታዋ በተቋሙ ምንም አይነት የጸጥታ ችግር ሳያጋጥማት ለምረቃ መብቃቷን ተናግራለች፡፡ “ከወሎ ህዝብና ከዩኒቨርሲቲው ያገኘሁትን አብሮነት፣ መቻቻል፣ አንድነትና ፍቅር ወደአካባቢዬ ስመለስ ህብረተሰቡን በማስተማር ለሰላም የድርሻዬን እወጣለሁ" ብላለች፡፡ “ተማሪዎች በአሉባልታ ወሬ ሳይታለሉ በትምህርታቸው ላይ ብቻ በማተኮር አገርና ቤተሰብ የጣለባቸውን አደራ መወጣት ይኖርባቸዋል” በማለትም አስገንዝባለች። ሌላው  ተማሪ ሀብቶም ገብረማርያም በዩኒቨርሲቲ ቆይታው አብሮነት፣ ፍቅር፣ መቻቻልና በጋራ የመኖር እሴት ማዳበሩን ገልጿል፡፡ ይህም ለስኬት እንዳበቃው የተናገረው ወጣቱ የአካባቢው ህዝብ በማስተማር ሰላምን ለማረጋገጥ ጠንክሮ እንደሚሰራ አመልክቷል፡፡ "ወጣቱ በሀሰት መረጃ በስሜት መነሳት እንደሌለበት ገልጾል ልዩነትን ከማጉላት ይልቅ እንደ ተማረ ኃይል ምክንያታዊ በመሆን መንቀሳቀስ ይኖርበታል" ብሏል፡፡ ልጆቻቸውን ለማስመረቅ ከመጡ ወላጆች መካከል አቶ ምህረቴ ተካ በበኩላቸው ልጃቸው በዩኒቨርሲቲ ቆይታው ትክክለኛ ኢትዮጵያዊ እሴትን ማጎልበቱን ነው የተናገሩት። “በቀጣይ ወደ አካባቢያቸው ሲመለሱ አቅመ ደካሞችን በመርዳት፣ በመደገፍና በመንከባከብ ለሌሎች አርያነት ያለው ተግባር ያከናውናል” ብለዋል፡፡ በክረምት በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ያደርገው የነበረውን ተሳትፎ ዘንድሮም አጠናክሮ እንዲቀጥል ከጎኑ በመሆን የሚያስፈልገውን እገዛ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል። የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አባተ ጌታሁን በበኩላቸው በዩኒቨርሲቲው በነበረው ሰላም ተማሪዎች ተረጋግተው፣ ተደማምጠውና ተረዳድተው በመንቀሳቀሳቸው ለስኬት መብቃታቸውን ገልጸዋል፡፡ በጸጥታ ችግር የወሎ ዩኒቨርሲቲ የመማር ማስማር ሂደት እንዳይስተጓጎል ህብረተሰቡ ላድረገው ከፍተኛ ድጋፍም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ ምሩቃን ተማሪዎች ወደ አካባቢያቸው ሲመለሱ በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ያዳበሩትን አንድነት፣ ፍቅርና ሰላም በማስጠበቅ የኢትዮጵያዊያንን የአብሮነት ባህል እንዲያስቀጥሉም አሳስበዋል። ተመራቂ ተማሪዎች ያገኙትን እውቀትና ሙያ በመተግበር አገርና ህዝብ የጣለባቸውን አደራ እንዲወጡም አስገንዝበዋል። "የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ድኤታ ዶክተር አህመዲን መሃመድ በበኩላቸው ምሩቃን ሥራ ፈላጊ ሳይሆኑ ሥራ ፈጣሪ በመሆን መንግስትን ማገዝ ይጠበቅባቸዋል" ብለዋል፡፡ “ልዩ ተሰጥኦ እና አዳዲስ ቴክኖሎጂ ፈጣሪዎችን በመደገፍና በማበረታታት ከፍተኛ ደረጃ እንዲደርሱም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የድርሻውን ይወጣል” ብለዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲው ደሴ ካምፓስ በተለያዩ የትምህርት መርሀ ግብሮች ያሰለጠናቸውን ከ3 ሺህ በላይ ተማሪዎች በነገው ዕለት እንደሚያስመርቅ ታውቋል። በተመሳሳይ ዜና የደሴ መምህራን ኮሌጅ በዲፕሎማ ያሰለጠናቸውን ከ2 ሺህ በላይ እጩ መምህራንን ዛሬ አስመርቋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም