ለአገር አቀፉ የ4 ቢሊዮን ችግኝ ተከላ ዘመቻ 4 ነጥብ 7 ቢሊዮን ችግኝ ተዘጋጅቷል

94
ሰኔ 29/2011 በክረምት ወራት ለመትከል በታቀደው የ4 ቢሊዮን ችግኝ ተከላ ዘመቻ ከ4 ነጥብ 7 ቢሊዮን በላይ ችግኝ መዘጋጀቱን አስተባባሪ ኮሚቴው አስታወቀ። አራት ሚኒስትሮችንና አንድ ኮሚሽነርን ያካተተው አስተባባሪ ኮሚቴ ጉዳዩን አስመልክቶ ዛሬ በሰጠው መግለጫ ለችግኝ ተከላው 1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሄክታር መሬት መዘጋጀቱን ይፋ አድርጓል። የአስተባባሪ ኮሚቴው አባላት የግብርና ሚኒሰትር አቶ ዑመር ሃሰን፣ የትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ጥላጌ ጌቴ፣ የውሃ፣መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ፣ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሃመድ እና የደንና አካባቢና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ኮሚነር ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ ናቸው። ተራራማ መልክዓ ምድር የበዛባት ኢትዮጵያ የቀድሞ ደን ሽፋኗ የተመናመነና አፈሯ እየታጠበ በመሆኑ የደን ሽፋኗን ለመመለስ፣ የዝናብ ስርጭቱን ለማስተካከል፣ የሙቀት ሁኔታውን ለማሻሻል የደን ሽፋን ሁኔታ መለወጥ እንደሚያስፈልግ በመግለጫው ተጠቁሟል። ''ኢትዮጵያ ለዓለም አረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ካዘጋጁ አገሮች አንዷና የመሪነት ሚናዋን እየተጫወተች ያለች አገር ናት' ያሉት የውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ ለክረምት ችግኝ ተከላ ዘመቻው ከ4 ነጥብ 7 ቢሊየን በላይ ችግኝ መዘጋጀቱ ጠቁመዋል። በኦሮሚያ 1 ነጥብ 9 ቢሊዮን፣ በአማራ 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን፣ በደቡብ 1 ነጥብ  4 ቢሊየን ችግኞች መዘጋጀታቸውን አመልክተዋል። እስካሁንም 1 ነጥብ 3 ቢሊየን ችግኞች የተተከሉ ሲሆን ከነዚህም መካከል በአማራ 280 ሚሊየን፣ በደቡብ 641 ሚሊየን፣ በኦሮሚያ 470 ሚሊየን ችግኞች ተተክለዋል ነው ያሉት። ሀምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም 'የዜጎች የአረንጓዴ አሻራ ቀን' በአንድ ጀምበር 2 ሚሊየን ችግኞችን በመተከል ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ አዲስ ክብረወሰን የምታስመዘግብበት ቀን እንደሚሆን ይጠበቃል። ዕለቱ በገጠርም ሆነ በከተማ ሁሉም ዜጋ በነቂስ ወጥቶ የሚሳተፍበት ብቻ ሳይሆን የውጭ አገር ዜጎችም በችግኝ ተከላው ተሳታፊ እንደሚሆኑበት ገለጸዋል። የኪነ ጥበበብ ባለሙያዎች፣ የመንግስት ሃላፊዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች በሰፊው እንደሚሳተፉ ገልጸው፤ የመገናኛ ብዙሃን በዘገባ ሽፋናቸው ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል። የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ፈቃዱ በየነ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ግንባታ ግቦች የ1 የሚሊዮን ሄክታር መሬት የደን ሽፋን እቅድ መኖሩን ጠቅሰዋል። ዘንድሮ የችግኝ ተከላ ዘመቻ ዛፎችን ተክሎ መመለስ ሳይሆን በዘላቂነት እንዲጸድቁ ተከላው በባለሙያ እንደሚታገዝ፣ ጸረ ተባይ መድሃኒትና ኮምፖስት እንዲዘጋጅና ችግኞቹ ከእንስሳት ንክኪ ነጻ እንዲሆኑ የሚደረግ መሆኑንም ገልጸዋል። በየአካባቢው የሚገኙ የግብርና ባለሙያዎች አስፈላጊውን ሙያዊ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ያቀረቡት ኮሚሽነሩ፤ የተተከሉ ችግኞችን ለአንድ ወገን የሚተው ሳይሆን ማህበረሰቡ በባለቤትነት ዘላቂ እንክበካቤ ማድረግ እንደሚጠበቅበት አስገንዝበዋል። የትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ጥላዬ ጌቴ ለችግር የተጋለጠውን ተፈጥሮ ያሁኑ ትውልድ ሊታደገው እንደሚገባ አብራርተዋል። የትምህርትና ስልጠና ማህበረሰቡ በክረምት ወራት የእረፍት ጊዜው በችግኝ ጉድጓድ ቁፋሮ፣ በማጓጓዝ፣ በመትከልና በመንከባከብ ተግባራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል። በከተሞች አካባቢ በተመረጡ ስፍራዎች ከ760 ሚሊየን ችግኞች ለመተከል መታቀዱን የገለጹት የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትሯ ኢንጅነር አይሻ መሃመድ በበኩላቸው 'የከተሞች አረንጓዴ ልማት ምርጫ ውስጥ የሚገባ ጉዳይ አይደለም' ብለዋል። ከተሞች ውብ፣ ጽዱ፣ አረንጓዴ፣ለቱሪስት ምቹ እንዲሆኑ ለማድረግ በነብስ ወከፍ 40 ችግኝ የመትከሉን ስራ እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ሁሉም ከተሜ እንዲሳተፍ ጠይቀዋል። የከተማ ችግኝ ጣቢያዎች፣ የግብርና ቦታዎች፣ የግለሰብና ተቋማት ግቢና አካባቢ፣ የሃይማኖት ተቋማት በአጠቃላይ 17 የከተሞች ስፍራዎች በአረንጓዴ ልማት የተለዩ መሆኑን ተናግረዋል። የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ዑመር ሃሰን የሚተከሉ ችግኞች የግብርናና ደንን ጥምረትን የያዙ ለምግብነትና ለካርበን ስበት የሚያገለግሉ እንደሆነ ገልጸዋል። አንድ አራተኛ የሚሆኑት ወይም አንድ ቢሊዮን ችግኞች የእንጨትነት ባህሪ ያላቸው አገር በቀል ችግኞች እንደሆኑ አመልክተዋል። የሚተከሉ ችግኞችን በመንከባከብ ረገድ ለአንድ ተቋም የሚተው ሳይሆን በርካታ ተቋማት በባለቤትነት በጋራ የሚተገብሩት እንደሚሆን ነው የተብራራው። እያንዳንዱ ዜጋ በነብስ ወከፍ 40 ችግኞች እንዲተክል ታሳቢ ያደረገ የ4 ቢሊየን ችግኝ ተከላ ዘመቻ ንቅናቄ መጀመሩ ይታወቃል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም