ዩኒቨርሲቲው በትምህርት ዘመኑ በነበረው ስኬታማ የሰላማዊ መማር ማስተማር እንቅስቃሴ ምስጋና ተቸረው

54
ሰመራ/ጎባ ሰኔ 29 ቀን 2011 የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ለሰመራ ዩኒቨርሲቲ በዓመቱ ላሳየው ስኬታማ የሰላማዊ መማር ማስተማር እንቅስቃሴ ምስጋናውን አቀረበ። የሰመራና የመዳወላቡ ዩኒቨርሲቲዎች በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠኗቸውን ከ5ሺህ በላይ ተማሪዎችን ዛሬ አስመርቀዋል። የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደ ማርያም ዛሬ በተካሄደው የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው በ2011 የትምህርት ዘመን ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት አርአያ ሆኖ ወጥቷል። የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች በወንድማማችንና እህትማማችነት መንፈስ የፈጠሩት ቤተሰባዊ ትስስር ችግሮች እንዳይፈጠሩ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አመልክተዋል። "እናንት የሉሲ ልጆች የሰላም አምባሳደሮች ናችሁ። ይህን በቀጣይ በምትሰማሩበት የሥራ መስክ አጠናክራችሁ ልትቀጥሉበትም ይገባል '' ሲሉም ሚኒስትሯ ተናግረዋል። ለዚህም ለዩኒቨርስቲው አመራር፣ ለአካባቢውን ነዋሪዎችና ለሰመራ-ሎጊያ ከተማ ከንቲባ በሚኒስቴሩ ስም ምስጋና አቅርበዋል። የሰመራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አደም ቦሬ ዩኒቨርሲቲው ችግሮችን በውይይት በመፍታት የሰላም አምባሳደርነቱን በተግባር ማሳየቱን አስታውቀዋል። የአፋር ክልል መንግሥትና የኅብረተሰቡ ድጋፍ የጎላ እንደነበርም ገልጸዋል። ዩኒቨርስቲውየቅበላ አቅሙን ወደ 15 ሺህ ከፍ የሚያደርጉለት የማስፋፊያ ግንባታ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን አስረድተዋል። ዩኒቨርሲቲው ባለፉት 10 ተከታታይ ዓመታት ከ12 ሺህ በላይ ተማሪዎችን አስመርቆ ለአገራዊ እድገቱ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑንም ፕሬዚዳንቱ አስታውሰዋል። ዩኒቨርሰቲው ዛሬ ለ10ኛ ጊዜ በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ ያስመረቃቸው ከ1 ሺህ 700 በላይ ተማሪዎችን ነው። ከተመራቂዎች መካከል ተማሪ ሊበን መሐመድ የዩኒቨርስቲው አመራርና የአካባቢው ኅብረተሰብ ለተማሪዎች የሚያደርገው ድጋፍና ክትትል ለሌሎች ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በምሳሌነቱ እንደሚጠቀስ ተናግራለች። ሌላው ተመራቂ አብዱልአዚዝ ሁሴን በትምህርት ቆይታው ወቅት ተማሪዎች እርስ በእርስ የነበራቸው መከባበርና መረዳዳት ለሰላማዊ የመማር ማስተማር እንቅስቃሴ አስተዋጽኦ እንደነበረው አስረድቷል። በተመሳሳይ የመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ለ11ኛ ጊዜ በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን ከ4 ሺህ ተማሪዎች ዛሬ አስመርቋል። ከተመራቂዎች መካከል 3 ሺህ 728 የሚሆኑት በመጀመሪያ ዲግሪ የሰለጠኑ ሲሆን፣ 268ቱ በሁለተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን የተከታተሉ መሆናቸው ታውቋል። 55 የሚሆኑት ተመራቂዎች በሜዲካል ዶክትሬት የተመረቁ ናቸው፡፡ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ሀብታሙ ተካ ምሩቃን በትምህርት ቆይታቸው ያገኙትን እውቀት ወደ ተግባር ቀይረው በአገሪቱ ምጣኔ ሀብታዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ እድገት አሻራቸውን እንዲያስቀምጡ አሳስበዋል። የዩኒቨርሲቲው የቦርድ አባል ወይዘሮ ሰዓዳ ከድር ምሩቃኑ ሥራ ጠባቂ ሳይሆኑ፣ ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ ጠይቀዋል፡፡ የመማር ማስተማር ሥራውን ከ12 ዓመታት በፊት የጀመረው ዩኒቨርሲቲ የዛሬ ምሩቃንን ሳይጨምርከ23 ሺህ 235 በላይ ተማሪዎችን ማስመረቁ በምረቃው ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም