መንግስት የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የያዘውን አቋም እንደግፋለን... በባሌ ዞን የሕብረተሰብ ክፍሎች

49
ሰኔ 28/2011  መንግስት የአገሪቱን የጸጥታ ችግሮች በመፍታት የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የያዘውን አቋም እንደሚደግፉ የባሌ ዞን የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ገለጹ። የዞኑ የሰላምና የልማት ኮንፈረንስ ዛሬ በባሌ ሮቤ ከተማ ተካሂዷል፡፡ የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች በመድረኩ ላይ እንደተናገሩት መንግስት በሀገሪቱ የሚታዩ የፀጥታ ችግሮችን በመፍታት የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የጀመረውን እንቅስቃሴ ይደግፋሉ፡፡ ከኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች መካከል የጎባ ከተማ ተወካይ ሼህ ኡመር ሉጎ መንግስት የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋቱና ሌሎች የማሻሻያ ሥራዎችን በመስራቱ ሊበረታታ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ይሁንና የመንግስትን ሆደሰፊነት ወደ ጎን በመተው ስልጣንን ከአግባብ ውጭ ለማግኘት ድብቅ የፖለቲካ አጀንዳቸውን በሚያራምዱ አካላት ላይ መንግስት እየወሰደ ያለው ህጋዊ እርምጃ በቂ እንዳልሆነም ገልጸዋል። እንደ ሼህ ኡመር ገለጻ መንግስት የሕግ የበላይነትን ለማስከበር ወደ ጠንካራ እርምጃ መግባት መጀመሩ ወቅታዊና የሚደግፉት ተግባር ነው። የአገሪቱን የፀጥታ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት በመንግስት በኩል የተያዘው አቋም እንዳስደሰታቸው የተናገሩት ደግሞ የጎሮ ወረዳ ተወካዩ አቶ አህመድ ሙክታር ናቸው፡፡ በተለይ ሕዝቡ ከስጋት ነፃ ሆኖ እንዲኖርና ህገወጥነት እንዲቆም መንግስት ጠንካራ የፀጥታ አደረጃጀት እንዲገነባ ጠይቀዋል፡፡ አቶ አህመድ እንዳሉት የክልሉን ሰላም ለማረጋገጥና የሕግ የበላይነትን ለማስከበር በመንግስት እየተወሰደ ያለውን እርምጃ በልበሙሉነት የሚደግፉትና የሚያደንቁት ተግባር ነው። በአካባቢያቸው የሕግ የበላይነትን በማስከበር ወንጀለኞችን ከማጋለጥ ጀምሮ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን የተናገሩት ደግሞ የጊኒር ወረዳ ተወካይ ወይዘሮ ፈጡማ አብደላ ናቸው፡፡ ኮንፈረንሱን የመሩት የባሌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኢብራሂም ሀጂ በበኩላቸው ህብረተሰቡ ህገወጥ ድርጊቶችን በማውገዝ እና በማስቆም መንግስት የህግ የበላይነት እንዲከበር እያደረገ ያለውን ጥረት እንዲደግፍ ጠይቀዋል። አስተዳዳሪው እንዳሉት፣ ኮንፈረንሱ ሀገራዊ ለውጡን ለማደናቀፍ በተለያዩ አካላት የሚደረጉ የጥፋት ሙከራዎችን ለማጋለጥና ህብረተሰቡ የሚያደርገውን ሁለንተናዊ ድጋፍ ለማጠናከር ጉልህ ድርሻ አለው፡፡ በተጨማሪም ለውጡ በስኬት እንዲቀጥል የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስና በየቦታው እያጋጠሙ ያሉ ተግዳሮቶችን በህብረተሰቡ ድጋፍ መከላከል ሌላው የኮንፈረንሱ ዓላማ መሆኑንም ነው አቶ ኢብራሒም ያስረዱት፡፡ ኮንፈረንሱ በክልሉ የህግ የበላይነትን በማስከበር በኩል ያገጠሙ ፈተናዎችና ቀጣይ ስራዎች ላይ ያተኮረ ባለ ሰበት ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቋል፡፡ ለአንድ ቀን በተካሄደው የሰላም ኮንፍረንሱ ላይ ከዞኑ 18 ወረዳዎችና ሁለት የከተማ አስተዳደሮች የተወከሉ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፏል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም